የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ግራ ማጋባቱን ቀጥሎአል

የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ ዜናዊ  በአ ገሪቱ የታየውን የገንዘብ ግሽበት ወደ አንድ አሀዝ እናወርዳለን ብለው በፓርላማ በተናገሩ በሳምንታት ውስጥ የምግብ ዋጋ በእጅጉ መጨመሩ ህዝቡን እያነጋገረ ነው።

በአማራ ክልል ጤፍ እስከ 1400 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑ  ህዝቡ በተለይም የመንግስት ሰራተኛው ምን እየሆነ ነው ማለት ጀምረዋል። የጤፍ መጨመር ሌሎች ምርቶችንም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምሩ አድርጓል።

የባህርዳር ዘጋቢያችን እንዳለው የአማራ ክልል ምክርቤት አባላት ጉዳዩን ወደ ፊት በመግፋት አሁን የሚታየው የኑሮ ውድነት ካልተቀረፈ ማህበራዊ ምስቅልቅል ሊፈጠር ይችላል በማለት ለክልሉ መገናኛ ብዙሀን ፍርሀታቸውን ገልጠዋል።

የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚህ አመት በቂ ምርት እንደተገኘና በቂ ምርት ወደ ገበያ መቅረቡን እየገለጡ የች ግሩ መንስኤ  ህገ ወጥ ነጋዴዎች እና ስግብግብ ነጋዴዎች እህሉን በመጋዘን በማከማቸታቸው በመሆኑ እርምጃ እንደሚወስዱ እየዛቱ ነው።

ዘጋቢያችን እንደገለጠው ከሆነ ግን ስግብግብ የተባሉት ነጋዴዎች በመጋዘናቸው ያለው መጠን የእርሻ ሰብል ከያዙት ጋር ፈጽሞ የሚወዳዳር አይደለም።

በተመሳሳይም መንገድ መንግስት በድጎማ የሚሸጠውን ስኳር በህገወጥ መንገድ ሸጠዋል በሚል ምክንያት ከ150 በላይ ሱቆችን አሽጓል።

እርምጃው የተወሰደው በአዲስ አበባ ውስጥ በሚሰሩ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ላይ ነው።

በጣም በሚያሳዝን አገር ውስጥ ነው የምንኖረው፣ እነርሱ ስኳር ከገበያ አጠፉ፣ እኛ ከየቦታው ስኳር አሰባስበን አንድና ሁለት ኪሎ እየሸጥን ልጆቻችንን ለማሳደግ ተፍ ተፍ እንላለን። በድንገት መጥተው ሱቄን አሸጉት፣ ይሄ ምን ይባል፣ ወዴትስ ይኬዳል?” ሲሉ እንባ እየተናነቃቸው ለዘጋቢያችን ገልጠዋል።

የሶስት ልጆች አባት የሆኑት ነጋዴው እንዳሉት አንድም ቀን ስኳር ከተመን በላይ ሸጠው አያውቁም፣ ለራሳቸው የሚያውሉትን ፍጆታ ከመሸጥ ውጭ አንድም በህገወጥ ስራ የተሰማሩበት ሁኔታ የለም። ያለምንም ማስረጃ ከመሬት ተነስተው ሱቄን አሸጉት በማለት አክለዋል።

መንግስት ስኳር ማቅረብ ካቃተው ለምን ለሌሎች አስመጪዎች ስራውን አይተወወም  የሚሉት ነጋዴው፣ እኛ ባላመጣነው ጣጣ ዳፋችን እየበላን ነው ሲሉ ገልጠዋል።

መንግስት በነጋዴው ላይ በሚወሰደው ያልተጠና እርምጃ ከነጋዴው ጋር በየጊዜው ሆድና ጀርባ እየሆነ ነው፤ በአቅርቦት ማነስ ለሚፈጠሩት ችግሮች መንግስት ሁሌም ነጋዴዎች ይወቅሳል። በርካታ ኢኮኖሚስቶች መንግስት የብር ምንዛሬ ዋጋ  እንዲወርድ ማድረጉ አሁን ለተፈጠረው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

11 በመቶ እድገት እንዳገኘ የሚናገረው የመለስ መንግስት አሁን የሚታየውን ከፍተኛ የሆነ የዋጋ አለመረጋጋት ማስቆም ካልቻለ፣ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል በማለት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ መካከለኛ ገቢ ካሉዋቸው አገሮች ተርታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንሰለፋለን፣ የሚሊኒየም የልማት ግቦችን እናሳከለን በማለት ከፍተኛ ፕሮፓጋንዳ ሲነገር ከሰነበተ በሁዋላ፣ የአለማቀፉ የልማት መርሀግብር ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች ከማያሳኩ አገሮች ተርታ እንደፈረጃት ታውቋል።

ውስጥ አዋቂዎች እንዳሉት በቅርቡ ይወጣል በሚባል ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ኢትዮጵያ የሚሊኒየሙን ግብ ከማያሳኩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ቀዳሚዋ ነች።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide