በጋምቤላ አለመረጋጋቱ እንደቀጠለ ነው

የካቲት 29 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጋምቤላው ዘጋቢያችን እንደገለጠው ሰሞኑን ኤለያ በሚባለው መስመር ታጣቂዎች የአንድ የግለሰብ እርሻን ሲጠብቁ በነበሩ ሶስት ዘበኞችና የእርሻው ባለቤት ላይ ጥቃት ከፍተው 3ቱ የአኝዋክ ተወላጅ የሆኑት ዘበኞች ወዲያው ሲገደሉ የእርሻው ባለቤት የሆኑት ሴት ባለሀብት ደግሞ በጸና ቆስለው ወደ አዲስ አበባ ተወስደው በመታከም ላይ ናቸው።

ታጣቂዎች የሚሰነዝሩት ጥቃት እያየለ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ የክልሉ ባለስልጣናትም ሆኑ የአላሙዲ ንብረት የሆነው የሳውዲ ስታርእና የህንዱ ካራቱሬ ሰራተኞች በፌደራል ፖሊስና በወታደር እየታጀቡ ስራቸውን ለመስራት ተገደዋል።

ዘጋቢያችን እንደሚለው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ ያለ ፌደራል ፖሊስ ወይን መከላከያ ሰራዊት አጀብ የማይታሰብ ነው፣ ከዚህ ቀደም የአላሙዲን ሰራተኞች ያለወታደራዊ አጀባ ስራቸውን አይሰሩም ነበር፣ አሁን ይበልጥ ጥበቃው ተጠናክሮአል።

የጋምቤላ አለመረጋጋት መንስኤ በሀይል ያለፍላጎታቸው እየተፈናቀሉ እንዲሰፍሩ የተደረጉት የአካባቢው ተወላጆች የሚፈጥሩት ተቃውሞ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስፍሯል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ    የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ፤በጋምቤላ የህወሀት/ኢህአዴግ ነፍጥ አንጋቾች በብረት ለበስና በከፍተኛ መኮንኖች በመመራት በየወረዳውና በየቀበሌው ህዝቡን እየሰበሰቡ አውጫጭኝ ጀምረዋል ብሎአል።

የጦር መኮንኖቹ ህዝቡን ሰብስበው፦”ሽፍቶቹ ስንት ይሆናሉ?”በማለት ላቀረቡት ጥያቄ አንድ አዛውንት ሲመልሱ፦” አንድ ቀን ከጠዋት እስከ ማታ ተሰልፈው ሲሄዱ ዋሉ። በጣም ብዙ ናቸው።ውሀ ለመቅዳት ወንዝ የወረዱ ሰዎችም አይተዋቸዋል።የሚሄዱት በተለያዩ አቅጣጫዎች ነው። ታጥቀዋል።ሙሉ የወታደር ልብስም ለብሰዋል”ብለዋል።

ከዚያም ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት መኮንኖች፦”ለሽፍቶቹ ምንም ዓይነት መጠለያ እንዳታደርጉ። ሲመጡም ምግብ እንዳትሰጧቸው”  በማለት ማስጠንቀቂያ ሢሰጡ፤ ተሰብሳቢው ህዝብ፦”ደኑ መጠለያቸው ነው፤ ጫካውም ምግብ ሞለረቶታል” በማለት እንደመለሰላቸው የንቅናቄው ምንጮች ከስፍራው ዘግበዋል።

በህዝቡ ምላሽ የተበሳጩ አንድ ከፍተኛ የ አገዛዙ መኮንንም ንዴታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው፦”ከእናንተ ጋር ጊዜዬን ማጥፋት አልፈልግም!”እስከማለት መድረሳቸው ተሰምቷል።

ይኸው አውጫጭን በተመሣሳይ ለወረዳ አስተዳደሮች ተመሣሳይ ጥያቄ በማቅረብ መካሄዱን የጠቀሰው የንቅናቄው መግለጫ፦መስተዳድሮቹ ከቀረቡባቸው ጥያቄዎች መካከል፦” አርሶአደሮቹ ለሽፍቶቹ ምግብ እንዲከለክሏቸው ለምን አላደረጋችሁም?፣ ሽፍቶቹ ከየትኛው ቀበሌ እና እነ ማን እንደሆኑ  አርሶ አደሮቹ እንዲጠቁሙ ለምን አላደረጋችሁም?” የሚሉት እንደሚገኙበት ጠቁሟል።

ላቀረቡት ጥያቄ የጠበቁትን ምላሽ ያላገኙት ገምጋሚዎቹም የወረዳ አስተዳደሮቹን በድክመት በመፈረጅ ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያስገድድ ሀሳብ አቅርበዋል።

በዚህም መሰረት በክልሉ ባሉት ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ተሿሚ ከነበሩት አስተዳደሮች ብዙዎቹ ከሀላፊነታቸው ተነስተዋል።

ከዚህም ባሻገር በተነሱት ሀላፊዎች ምትክ የተሾሙ አንድ ሰው፦”ነግ በኔ” በማለት ሹመቱን አልቀበልም ማለታቸውን የጠቀሱት ምንጮቹ፤ በክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ አለመተማመን፣ ሥጋትና ውጥረት መስፈኑን አመልክተዋል።

በ አካባቢው ሰፊ የእርሻ መሬት በመውሰድ እየተንቀሳቀሱ ያሉት የሳኡዲ ስታርና ሌሎች የውጪ ኩባንያዎች፤ የ አካባቢው ሰላም ለህይወታቸው አስጊ በሆነበት ሁኔታ በሥራቸው ሊቀጥሉ እንደማይችሉ መናገራቸው ተሰምቷል።

በጋምቤላ እየተፈፀመ ባለ ተደጋጋሚ ጥቃት ከፍተኛ የመንግሰት ባለሥልጣናት ጭምር እንደተገደሉ መዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide