ሼክ አላሙዲን በአፍሪካ አንደኛ ባለሀብት ተባሉ

የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የሚገኙ የወርቅ ጉድጓዶችን እንዲሁም የነዳጅ ማውጫ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት ሼክ አላሙዲን በአፍሪካ አንደኛ ባለሀብት ተባሉ

የኢህአዴግ ደጋፊ የሆኑት ቢሊየነሩ ሼክ ሙሀመድ አላሙዲን ይህን ማእረግ ያገኙት ናይጄሪያዊውን ቢሊየነር አሊኮ ዳጎቴን በመተካት ነው። የሼኩ አዲሱ የሀብት መጠን 12 ቢሊዮን 500 ሚሊየን ደርሷል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ታላለቅ የንግድ ተቋማትን በርካሽ ዋጋ በመግዛት የሚወነጀሉት ሼክ አለሙዲን፣ ሚድሮክ ወርቅ በተባለው ኩባንያቸው አማካኝነት በቅርቡ 33 ሺ ኪሎግራም ወርቅ አግኝተዋል። በሼክ አለሙዲን በመላ አገሪቱ እጅግ ሰፋፊ የሆኑ የእርሻ ቦታዎችንም ተቆጣጥረው ይዘዋል።

አልአሙዲን በ1980ዎቹ መጨረሻ ኢትዮጵያን ሲረግጡ የነበራቸው ሀብት ከ800 ሚሊዮን እስከ 1 ቢሊየን እንደሚገመት እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ። ሼኩ ሸራተንን ሲገነቡ ገንዘብ ሁሉ ያጥራቸው እንደነበር ከእርሳቸው ጋር ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጅ በአለም ዋጋ የታየውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ይህ ሀብታቸው በተከታታይ 5 አመታት በሶስት እጥፍ ማደጉ ይነገራል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎችን ከገዙ በሁዋላ፣ የሀብታቸው መጠን በብዙ እጥፍ መጨመሩም ይታመናል።

ሼክ አላሙዲ እያፈሩት ያለው ሀብት በአገሪቱ ውስጥ አወዛጋቢ እንደሆነ ነው። ሼኩ ከኢትዮጵያ የሚያገኙትን ያክል ገንዘብ ለኢትዮጵያ አልሰሩላትም እየተባሉ ይወቀሳሉ። በምርጫ 97 ወቅት አላሙዲን ኢህአዴግን ደግፈው በአደባባይ በመታየታቸው፣ ህዝቡ አይንዎን ላፈር ብሎአቸው ነበር። በቅርቡም አፌን ሳልከፍት ተሰደብኩ ብለው መናገራቸው ይታወሳል።

የ67 አመቱ አዛውንት በአለም 61ኛ ው ሀብታም ናቸው። ወደ ኢትዮጵአ ከመምጣታቸው በፊት ደረጃ ውስጥ ስለመግባታቸው የታወቀ ነገር የለም፣ ይሁን ከአምስት አመት በፊት 256ኛ ደረጃ ላይ ይገኙ እንደነበር ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide