(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 15/2010) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች በሽርክና ይተላለፋል መባሉ እንዳሳሰባቸው የኤርፖርቶች ድርጅት የቀድሞ ሰራተኞች ገለጹ።
ሰራተኞቹ ስጋታቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በ2009 በጸደቀው አዋጅ መሰረት በመቀላቀሉ ነው።
በየትኛውም ዓለም የኤርፖርቶች ድርጅት ከመንግስት ቁጥጥር ስር አይወጣም ሲሉም ያክላሉ።
የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ታላላቅ የመንግስት ተቋማትን በሽርክና ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሃብቶች ለማዘዋወር ውሳኔ ማሳልፉ ይታወሳል።
በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይታላልፋል መባሉ ለብዙዎች መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኖ ወጥቷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰራተኞች ያላቸውን ስጋት በግልጽ ማስቀመጥ ጀምረዋል።
የስጋታቸው ምንጭ ደግሞ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከአየር መንገድ ጋር የተቀላቀለ በመሆኑ ይህ የአንድን ሀገር ቁልፍ ለሌላ አሳልፎ እንደመስጠት ይቆጠራል በሚል ነው።
የኢትዮጵያ ፓርላም በቁጥር 406/2009 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለማቋቋም በወጣ ደንብ ሁለቱ ድርጅቶች ተቀላቅለዋል።
ለ20 ዓመታት በኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ውስጥ ያገለገሉት አቶ ይልማ አድማሱ እንደሚሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሸጣል ሲባል በአዋጅ የተጠቃለለው ኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን የሚያካትት ነው።
ስለዚህ ተቋሙ በሽርክና ከመተላለፉ በፊት ሁለቱን ድርጅቶች ያዋሃደው ደንብ መነሳት አለበት ሲሉም ይናገራሉ ።
በየትኛውም ዓለም ኤርፖርቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ይተዳደራሉ ያሉት አቶ ይልማ የኢትዮጵያ ፓርላማ ግን የዓለም ሁኔታን ባላገናዘበ መልኩ ይህን ውሳኔ አሳልፏል።
ሁለቱ ታላላቅ ድርጅቶች አንድ ላይ መቀላቀላቸው ለዘረፋ እንዲመች ሆን ተብሎ የተደረገ ነው የሚሉት ተቆርቋሪዎቹ በአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚመሩ በመሆናቸው ዘረፋና ሌብነቱ በጉልህ የሚታይበት እንደሆነም ያነሳሉ።
የኤርፖርቶች ድርጅት በሀገር ወስጥ ያሉትን ኤርፖርቶች በአጠቃላይ የሚያስተዳደር በቢሊየን የሚቆጠር ገቢን የሚያገኝ በመሆኑ ከፍተኛ ዘረፋ ይካሄድበታል በማለት ይናገራሉ
ድርጅቱ ከተለያዩ ዘርፎች የሚያገኛቸውን ገቢዎች የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩ ለዘረፋ ምቹ ነው ሲሉ የሚካሄደውን ሌብነትና ዘረፋ ያብራራሉ።
አሁንም ሰራተኞች እንደሚሉት ድርጅቱ በአየር መንገዱ ስር ከተጠቃለለ በኋላ በርካታ ሰራተኞች ደሞዝ ይከፈላቸዋል እንጂ ስራን እየሰሩ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
ተቋሙን የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ብቻ ተቆጣጥረውታል በማለትም ይናገራሉ ።