ህወሃት የሰማዕታት ቀን በሚል የሚከበረውን በአል የተቃውሞ መገለጫ አድርጎት ዋለ

ህወሃት የሰማዕታት ቀን በሚል የሚከበረውን በአል የተቃውሞ መገለጫ አድርጎት ዋለ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) ዛሬ የትግራይ ሰማዕታት ቀን በሐውዜን ከተማ በተከበረበት እለት የተያዙት መፈክሮች ህወሃት በቅርቡ የኢትዮ- ኤርትራን የሰላም ስምምነት በተመለከተ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያሳለፈውን ውሳኔ በመተቸት ያወጣውን መግለጫ የሚያንጸባርቁ ናቸው። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ያልተሳተፉበት ሰላም ዘላዊ ሰላም አይሆንም፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ህዝቦች ለዘላቂ ሰላም ጣምራ ክንድ እንፍጠር የሚሉት መፈክሮችን ሰልፈኞቹ ይዘው ወጥተዋል።
እንዲሁም ዶ/ር አብይ የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ አይደለም በማለት በፓርላማ ላይ ለተናገሩት ንግግር ምላሽ በሚመስል መልኩ “ ህወሃት የትግራይ ህዝብ የትግል ፍሬ ነው፣ ህዋሀት በልጆቻንን ደም የተገነባ ድርጅት ነው” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ወጥተዋል።
ዶ/ር አብይ “ህወሃትና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደለም” በሚል የተናገሩት ንግግር በርካታ ነባር የህወሃት መሪዎችን ማስቆጣቱን ምንጮች ይገልጻሉ። ንግግሩ አመራሩን ከትግራይ ህዝብ ለመነጠል ተብሎ የተደረገ ንግግር ነው በማለት የህወሃት አመራሮች ቅሬታቸውን እየገለጹ እንደሚገኙ የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።