በቄለም ወለጋ ዞን የሚታዬው ውጥረት አለመቀነሱን የአማራ ተወላጆች ተናገሩ

በቄለም ወለጋ ዞን የሚታዬው ውጥረት አለመቀነሱን የአማራ ተወላጆች ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) በ1977 ዓም በነበረው ድርቅ ከወሎ ክፍለ ሃገር ተሰደው በቄለም ወለጋ መቻራ ዙሪያ የሚኖሩ አርሶአደሮች ለኢሳት እንደተናገሩት ትናንት ከጠዋት ጀምሮ እስከ ቀኑ 10 ሰዓት ድረስ አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ በሚሉ ወጣቶችና በእነሱ መካከል በነበረው ግጭት 11 ሰዎች ቆስለዋል። ግጭቱን ለማብረድ አባገዳዎች ጣልቃ ገብተው ለማስቆም ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እንደቀረ አርሶአደሮቹ ተናግረዋል። ዛሬ የአካባቢው ፖሊሶች መጥተው ህዝቡን ቢያወያዩም መፍትሄ ሊያመጡ አለመቻላቸውን አርሶአደሮች ገልጸዋል።
ከድርጊቱ ጀርባ የታጠቁ ሃይሎች እንዳሉ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ሰዓት የስጋት ኑሮ እየኖሩ እንደሆኑ ገልጸዋል። የኦሮምያና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ሄደው እንዳልጠየቁዋቸውም ተናግረዋል።
በቅርቡ የኦህዴድና አማራ ክልል ባለስልጣናት ባህርዳር ላይ ተነጋግረው ከኦሮምያ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የተሰደዱት በቅርቡ ወደ ክልሉ እንደሚመለሱ ተናግረው ነበር። ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት ሆነዋል የተባሉ በርካታ የኦሮምያ ክልል የወረዳ አመራሮች መባረራቸውን እንዲሁም ከእንግዲህ ወዲህ ዜጎች ከክልሉ እንደማይፈናቀሉ ፕሬዚዳንቱን አቶ ለማ መገርሳን በመጥቀስ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ አቅርበው ማቅረባቸው ይታወቃል።