የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት ሊከፈል ነው

የካቲት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ሁለት ቦታ ለመክፈል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በቂ ጥናት ያልተደረገበትና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ባለመሆኑ መንግሥት ዕርምጃውን  እንዲገታ እና ዳግም እንዲያጤን  በዓለማቀፍ አበዳሪዎች መጠየቁን ሪፖርተር ዘገባ።

እንደ ጋዜጣው ዘገባ የዓለም ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎች ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችም ኮርፖሬሽኑ የመዋቅር ለውጥ የሚደረግበት ከሆነ ብድር ላለመስጠት እያንገራገሩ ናቸው፡፡

መንግስት በአሁኑ ጊዜ ኮርፖሬሽኑን ለሁለት በመክፈል፦” የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን “  እና “ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ኮርፖሬሽን” የሚባሉ ሁለት ራሳቸውን የቻሉ ኩባንያዎች በመመሥረት ሒደት ላይ ነው፡፡

ዋናውን ኮርፖሬሽን ሁለት ቦታ ከመክፈል ይልቅ ውስጣዊ መዋቅሩን በማሻሻል፣ በማጠናከርና የባለሙያዎችን አቅም በመገንባት ራሱን አስችሎ የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማስቀጠል የተሻለ እንደሆነ የዘርፉ ሙያተኞችና ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ቢመክሩም፤መንግስት ግን ከጀመረው የመክፈል እንቅስቃሴ ሊገታ አልቻለም።

ዓለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማቱ ደግሞ ኮርፖሬሽኑን ለሁለት ለመክፈል የሚደረገውን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ከማየት ባሻገር የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ኃላፊዎችን ማብራሪያ እየጠየቁ ሲሆን፤ እንደ ዓለም ባንክ የመሳሰሉ አበዳሪዎች ደግሞ የተሰጣቸው ማብራሪያ ያላረካቸው በመሆኑ፣ ለኮርፖሬሸኑ እየተደረገ ያለው የመዋቅር ለውጥ እንዲቋረጥ እያሳሰቡ ናቸው፡፡

ጋዜጣው እንዳለው ፤የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሁለት ቦታ እንዲከፈል ሐሳቡ የመጣውና ጥናቱ ተግባራዊ የተደረገው በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካይነት መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸው፣ በሚኒስቴሩ የተሠራው ጥናት የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያላገናዘበ ነው ይላሉ፡፡

የዘርፉ ሙያተኞች  ኮርፖሬሽኑ ሁለት ቦታ በሚከፈልበት ጊዜ የኃይል ማስተላለፍ ሥራ የሚያከናውነው ተቋም ማኔጅመንት ለውጭ ኩባንያ እንዲሰጥ እንደሚደረግ የተገለፀ ቢሆንም፤ ዓለም አቀፍ አበዳሪዎች በራሳቸው ፖሊሲ መሠረት ይህንን ዓይነቱን አካሄድ አይቀበሉም ይላሉ፡፡

ኮርፖሬሽኑ እንደበፊቱ አንድ ሆኖ መዋቅሩን እያጠናከረ ልክ ኢትዮ ቴሌኮም እንዳደረገው ለተወሰነ ጊዜ የኃይል ማስተላለፍ ተቋሙ ማኔጅመንት ለውጭ ኩባንያ በኮንትራት ቢሰጥ ትክክል ይሆናል የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ኮርፖሬሽኑ ሁለት ቦታ ከተሰነጠቀ በኋላ  የሚሰጥ ከሆነ ግን የአበዳሪዎችን አመኔታ ያጣል ይላሉ፡፡

በተለይ ዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኮርፖሬሽኑን ሁለት ቦታ ለመክፈል የተደረገው ጥናት በጥድፊያና በግብታዊነት የተወሰነ በመሆኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ትክክል ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ፣ ኮርፖሬሽኑ ለወሰዳቸው ብድሮች ዋስትና ስለማይኖርና የሕግ ክፍተት ስለሚፈጥር ገንዘባቸው አደጋ ውስጥ የሚወድቅ ይመስላቸዋል በማለት የሥጋቱን መጠን ይገልጻሉ፡፡

ኮርፖሬሽኑን ሁለት ቦታ የመክፈል ሐሳብ መጥቶ ወደ ተግባር የተገባው በባለሙያዎች በሚገባ ተጠንቶበት ሳይሆን በይድረስ ይድረስ በቀረበ ጥናት ላይ የፖለቲካ ውሳኔ ስለተሰጠበት ነው ሲሉም ይተቻሉ፡፡

የዓለም ባንክም ሆነ የአፍሪካ ልማት ባንክ ከበርካታ አበዳሪ ተቋማት አምጥተው የሚሰጡትን ብድር ሁለት ቦታ ለሚከፈል ድርጅት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸው፣ አገሪቱ ከምታገኛቸው የውጭ ብድሮች ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ብድር ለኢነርጂ ሴክተር በመሆኑ መንግሥት ውሳኔውን ሊያጤነው ይገባል ሲሉ ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሐምሌ 2002 ዓ.ም. ኮርፖሬሽኑ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የደረሱበት ደረጃ ለማድረስ ጥናት እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠታቸውን የሚያስታውሱ አንድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ባለሙያ፣ ሐሳቡ ፈሩን ስቶ ሄዶ ወደ አላስፈላጊ ውሳኔ እንደተደረሰ ያስረዳሉ፡፡

የሌሎች አገሮች ልምድ እንደሚያስረዳው  እስከ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ኩባንያዎች እንኳን ይህንን ዓይነቱን ዕርምጃ አያስቡትም  አያስቡትም ያሉት ባለሙያው፤ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ከውጭ ከፍተኛ ብድር እያስፈለገ ባለበት ወቅት ኮርፖሬሽኑን ሁለት ቦታ ሰንጥቆ የአበዳሪዎችን አመኔታ ማጣት ከባድ ነው ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡
አበዳሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ያበደሩ እንደመሆናቸው መጠን ኮርፖሬሽኑ ለሁለት ሲከፈል የወደፊቱን የመክፈል አቅምና ያበደሩትም ሆነ ለማበደር እየተዘጋጁ ያሉትን ገንዘብ የትኛው መዋቅር እንደሚከፍላቸው ጥያቄ ከማንሳታቸውም በላይ ባለፉት ሳምንታት ተቋማቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርን ማብራርያ ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንዳለ የኃይል ሥርጭት ተቋም ማኔጅመንት የእስራኤል ኩባንያ  እንደሚረከብ ቀደም ሲል ቢገለጽም፣ አሁን በተገኘው መረጃ  “ኢንዲያን ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን” የተባለ የህንድ ኩባንያ ጨረታውን ሊያሸንፍ እንደሚችል እየተነገረ መሆኑን ነው ጋዜጣው  ጨምሮ የዘገበው።

በመሆኑም በቅርቡም ከህንዱ ኩባንያ ጋር የማኔጅመንት ኮንትራት ስምምነት እንደሚፈረም ምንጮች  ገልጸዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ክላስተር ኃላፊና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል የሚመሩት የኮርፖሬሽኑ ቦርድ፣ ጨረታው በሚገባ ተካሂዶ ተወዳዳሪዎቹ በሚገባ ከተመረመሩ በኋላ የህንዱ ኩባንያ ተሽሎ እንደተገኘ መናገራቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡

የፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ሊቀመንበር ህንዳዊው አር.ኬ. ናያክ  በበኩላቸው ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኩባንያቸው ለሁለት ዓመታት የሚቆይ የ16 ሚሊዮን ዶላር የማኔጅመንት ኮንትራት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ጋር እንደሚፈራረም አስታውቀዋል፡፡