የኤሌክትሪክ ኃይል ለተከታታይ ቀናት መቆራረጥን ተከትሎ በአዲስ አበባ የዳቦ እጥረት እና ከወትሮው በተለየ መልኩ የውሃ ስርጭት መስተጓጎል ተከሰተ፡፡

ኀዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፉት አራት ቀናት በተከታታይ በመላ ሀገሪቱ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ተከትሎ ዳቦ ቤቶች በሙሉ አቅማቸው መስራት ባለመቻላቸው በርካታ ዳቦ ቤቶች ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
አንድ የሁለት ልጆች አባት እንደሆነ የተናገረ ነዋሪ ሰሞኑን ዳቦ ቤቶች ጠዋት አንድ ሰዓት ግድም ጀምሮ ዳቦ አልቆአል ስለሚሉ ልጆቹ ቁርሳቸውን ሳይመገቡ እንደሚያረፍዱ ጠቅሶአል፡፡ ያነጋገርናቸው የዳቦ ቤቶች ባለቤቶች የመብራቱ መቆራረጥ ስራቸውን በማስተጓጎሉ በቂ ምርት ለገበያ ማቅረብ እንዳላስቻላቸውና በዚህም ሁኔታ በዋጋ ተመን የሚያቀርቡት ዳቦ በብዛት መሸጥ ካልቻሉ ስለማያዋጣቸው ዋጋ ለመጨመር እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም አምራቾች በጋራ ሆነው ለሚመለከታቸው መንግስታዊ መ/ቤቶች አቤቱታ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡
በበለስና ግልገል ጊቤ አንድ የሃይል ማመንጫዎች የቴክኒክ ችግር በማጋጠሙ ሃይል ጠፍቶ መክረሙንና ችግሩ መስተካከሉን የሚመለከታቸው መ/ቤቶች ቢናገሩም አሁንም የሃይል መቆራረጡ መቀጠሉን ጠቅሰው በዛሬው እለት እንኩዋን ከማለዳ ጀምሮ ቢያንስ ለአራት ሰኣታት መብራት እንዳልነበረ ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥባቸው አብዛኛው አካባቢዎች የውሃ ስርጭትም ስለሚስተጓጎል የችግሩ መደራረብ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ነዋሪዎች በምሬት እየተናገሩ ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች በሃይል መቆራረጥ ምክንያት ምርት ለማምረት በማይችሉበት ደረጃ በመድረሳቸው ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደብዳቤ ጽፈዋል። አንዳንድ ድርጅቶች ጄኔሬተር ለመጠቀም በመገደዳቸው ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል።
ኢሳት አንዳንድ የውጭ አገር ኩባንያዎች የጻፉዋቸውን ደብዳቤዎች ቅጅ የደረሰው ሲሆን፣ ኩባንያዎች በመብራት ምክንያት የደረሰባቸውን ኪሰራ ዘርዝረው አቅርበዋል።
አንድ የቻይና የቆዳ ፋብሪካ ኩባንያ ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት ሶስት ወራት ብቻ ለ58 ቀናት 305 ሰአታት መብራት እንደጠፋበት ገልጾ፣ በተለይ መብራት የሚጠፋበት ቆዳውን በኬሚካል በሚነከርበት ወቅት በመሆኑ የምርት ጥራቱን በማበላሸቱ ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ እንዳልቻለ ገልጿል። እስካሁን ድረስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መክሰሩን የገለጸው ኩባንያው፣ በአሁኑ ወቅት ስራውን ከ20 በመቶ በታች በሆነ አቅሙ ለማምረት መገደዱን አስታውቋል። የኤሌክትሪክ ሂሳብ ቀደም ሲል ሲጠየቁ ከነበረው በ4 እጥፍ በመጨመሩ ስጋት ላይ እንዲወድቁ እንዳደረጋቸውም ኩባንያው በደብደባው አስታውቋል።
በሌላ በኩል ድግሞ መንግስት ሁለተኛውን የእድገት እቅድ ለሰራተኛው ለማወያየት በጠራው ስብሰባ ሰራተኛው ለ 2 ቀናት ስራ እንዲያቆም በመደረጉ ተጨማሪ ችግር መፈጠሩን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። ፋብሪካዎቹ ለሰራተኞች በስብሰባዎች ለሚሳተፉባቸው ቀናት ደሞዝ እንዲከፍሉ ተገደዋል። መብራት እየጠፋ ለኪሳራ የተዳረጉት ፋብሪካዎች፣ ለ2 ቀናት መንግስት በጠራው ስብሰባ እንዲሳተፉ ለተደረጉት ሰራተኞችም ክፍያ ፈጽሙ መባላቸው ተጨማሪ ችግር እንዲፈጠረባቸው ምንጮች አክለው ገልጸዋል።