የኢንደስትሪያል ዞን ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መቱ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 7/2010)በአዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ዞን በሚገኙ ፋብሪካዎች የሚሰሩ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ መምታታቸው ተገለጸ።

አድማ በመምታታቸው ከመንግስት በኩል ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው ነው።

ፋይል

በሌላ በኩል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች ደሞዝ ሳይከፈላቸው ከአንድ ወር በላይ እንደሆናቸው ተገልጿል ።

አዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያል ዞን ባለፉት ሶስት ቀናት ባልተለመደ መልኩ ውጥረት ታይቶበታል።

በርከት ያሉ በውጭ ባለሀብቶች የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች ከወትሮው ተግባራቸው ተገተዋል።

ሰራተኞች አድማ ላይ መሆናቸውን ይገልጻሉ። የኢሳት ወኪል ያነጋገራቸው አንዳንድ ሰራተኞች የደረሰባቸውን ግፍ ሲገልጹ እንባ ይቀድማቸዋል።

በአረብ ሀገራት ኢትዮጵያውያን ላይ ከሚደርሰው በደል የከፋ ነው ይላሉ። ሰራተኞችን ለአድማ ያበቃቸው የደሞዝ ክፍያ እጅግ ያነሰ፣ የኑሮ ደረጃን የማይመጥን፣ ዝቅተኛ ነው በሚል የተነሳው ጥያቄ ቢሆንም በፋብሪካው ባለቤቶች የሚፈጸመው የጉልበት ብዝበዛና የሚፈጸመው በደልም ተጠቅሷል።

ሰራተኞቹ በኢንዱስትሪ ዞኑ የሚታየው የሰራተኛ አያያዝ የባሪያ ስርዓትን የሚያስታውስ ነው ይላሉ።

ሰራተኛው መብቱ ተጥሶ ሰብዓዊ ክብሩ ተዋርዶ የሚሰራበት ነው የሚሉት ሰራተኞቹ አንዳንድ የውጭ ባለሀብቶች በአካል በመምጣት ሰራተኛው ላይ ድብደባ እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።

ሰራተኞቹ ተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም።

የመንግስት ባለስልጣናት ከባለሀብቶቹ ጋር በምሆን ይበልጥ ጥቃት እየሰነዘሩብን ነው የሚሉት ሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ መጠየቃቸው እንደወንጀል ተቆጥሮ ከፍተኛ ወከባና ዛቻ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም ጥያቄአቸውን ምላሽ ባለማግኘቱ የስራ ማቆም አድማ መምታቸውን ሰራተኞቹ ገልጸዋል።

ዛሬ ሶስተኛ ቀናቸው ሲሆን በኢንዱስትሪ ዞኑ የሚገኙ ፋብሪካዎች ከምርት ውጭ ለመሆን መገደዳቸውን የኢሳት ወኪል ካደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪያን ዞን በአሁኑ ወቅት በፌደራል ፖሊስ የተወረረ ሲሆን አስተባባሪ ናቸው በሚል የተወሰኑ ሰዎች መታሰራቸውም ታውቋል።

በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ዞን የሚገኙ ሰራተኞች ለኢትዮጵያ ህዝብ አቤቱታችን ይድረስ ሲሉም ማስታወቃቸውን ወኪላችን ገልጿል።

በሰራተኞች የሚነሳ የክፍያና የመብት ጥያቄ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የኢንዱስትሪ መንደሮችም በስፋት መኖሩን መረጃዎች ያሳያሉ።

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ መንደር ሰራተኞችም ተመሳሳይ ጥያቄ በማንሳት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በአብዛኛው በውጭ ባለሀብቶች የሚመሩት በኢንዱስትሪ መንደር የሚገኙ ፋብሪካዎች በዝቅተኛ ክፍያ ጉልበት የሚበዘብዙ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይነሳል።

በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ለጥያቄው ምላሽ እንዲሰጥ ከማድረግ ይልቅ ከባለሀብቶቹ ጋር በመደረብ በሰራተኞቹ ላይ በደል ሲፈጽም እንደሚታይ ነው ሰራተኞች የሚገልጹት።

በሌላ በኩል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሰራተኞች ደምወዝ ሳይከፈላቸው 45 ቀናት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲ የማራኪ፣ቴዎድሮስ፣ ፋሲልና፣የጠዳ ካምፓሶች ያሉ መምህራን ከፍያ  አልተፈፀመም ከደሞዝ  ውጪ  የተለያዩ ጥቅማጥቅም ክፍያ  ቆሟል በሚል ተቃውሞ አንስተዋል።

በዩኒቨርስቲው በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

ለአስተዳደር ሰራተኞች ብቻ ካለው ገንዘብ የተከፈላቸው መሆኑን የሚጠቅሱት የኢሳት ምንጮች ለመምህራንና ለአብዛኛው የዩኒቨርሲቲው ሰራተኛ ግን ሳይከፈል ሁለተኛ ወር መድረሱን ለማወቅ ተችሏል።

ጉዳዩን ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን ብናሳውቅም ድምጻችን ታፍኗል ሲሉም መምህራኑና ሰራተኞቹ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።