ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ቢቢሲ እንደዘገበው ከ3 ሺ እስከ 5ሺ የሚገመተው የኢትዮጵያ ጦር አብዛኛውን የበለደውይን ከተማ ተቆጣጥረዋል። የኢትዮጵያ ጦር ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም ውጊያ መክፈቱንም የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጠዋል።
በለደወይን ወደ ሞቃዲሾ የምትወስድ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ድንበር መካከል የምትገኝ ስትራቴጂክ ከተማ ናት። ቢቢሲ እንደዘገበው በእስካሁ ጦርነት 20 የኢትዮጵያ ወታደሮች እና የአልሸባብ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
አልሸባብ ባለፈው ነሀሴ ወር ከሞቃዲሾ መውጣቱን አስታውቆ ነበር።
የአልሸባብ ቃል አቀባይ ኢትዮጵያ የሰነዘረቻቸውን ሶስት ጥቃቶች መክተው መመለሳቸውን እና የመልሶ ማጥቃት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጧል።
አልሸባብ ከኬንያ ጦር በደቡብ፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከኢትዮጵያ ጦር ደግሞ በመሀል አቅጣጫዎች ጦርነት ተከፍቶበታል።
አንድ የበለደወይን ነዋሪ ለሮይተርስ እንደገለጠው አልሸባብ ከበለደወይን ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ወጥቷል።
ለወራት የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ አለመግባቱን ሲናገሩ የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን ፣ ጦራቸው አልሸባብን በመደምሰስ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን ገልጠዋል።
የኢትዮጵያ ጦርም መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
የአልሸባብ ቃል አቀባይ ግን ከተማዋን ለቀው የወጡት የኢትዮጵያ ጦር በጅምላ የመድፍ ጥቃት በመክፈቱ ነው ይላሉ።
የኢትዮጵያ ጦር ከአምስት አመታት በፊት ወደ ሶማሊያ ገብቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት መውጣቱ ይታወሳል።
ሶማሊያውያን አልሸባብን ቢጠሉም፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ አገራቸው መግባቱን ግን አይደግፉም።
የሶማሊያ የሽግግር መንግስት በበኩሉ “ከኢትዮጵያ ባገኘነው ድጋፍ አንዳንድ በአልሸባብ ይዞታ ስር የነበሩ ቦታዎችን ተቆጣጥረናል”ሲል፣ የኢትዮጵያ ጦር ወደ አገራቸው የገባው በሽግግር መንግስቱ ጥያቄ መሰረት መሆኑን የሚገልጥ መግለጫ አውጥቷል።
አልሸባብ ምናልባትም በሶስት አቅጣጫዎች በተከፈተበት ጦርነት ሙሉ በሙሉ ሊዳከም ይችላል የሚሉ አስተያየቶች በመገናኛ ብዙሀን እየቀረቡ ነው።