በአየር ጤና አካባቢ የሚገኙ ሙስሊሞች እየደረሰ ያለውን ጭቆና እንደሚቃወሙ ባወጡት መግለጫና በአሰባሰቡት ፊርማ አስታወቁ

21 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በአየር ጤና አካባቢ የሚገኙ ከ1 ሺ በላይ የአንሳር መስጂድ አባላት ፣ በሙስሊሞች እየደረሰ ያለውን ጭቆና እንደሚቃወሙ ባወጡት መግለጫና በአሰባሰቡት ፊርማ  አስታወቁ::

ሙስሊሞቹ ታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓም ለኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ስራ አስፈጻሚ በጻፉት ደብዳቤ ” የህገ መንግስቱ ቁልፍ ድንጋጌዎች የሆኑት አንቀጽ 9/10/27ን በሚቃረን መልኩ የሙስሊም ዜጎችን የሀይማኖት በነጻነት ማራመድ የሚጋፉ ድርጊቶች እየተፈጸሙብን ይገኛል። “ብለዋል።

ሙስሊሞቹ አክለውም ” በተለይ የህዝብ ውክልና የሌለውና መንግስትና ሙስሊሙን ህብረተሰብ ሁሌም በሚያራርቅ ተግባር ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ወይም መጅሊስ ይህ አልበቃ ብሎት ከአንድ እስላማዊ ተቋም በማይጠበቅ ሁኔታ ሀይማኖታችንን ከፋፋይ የሆነ በተግባርም ሊባኖስን ሲያተራምስ የነበረውን አህባሽ የተባለ አስተሳስብ ከማራመድ ባለፈ ህዝበ ሙስሊሙ በግድ እንዲቀበል ይህንን የማያደርግ ሁሉ አክራሪ፣ አሸባሪ ጸረ ሰላም ወሀብያ ወዘተ በየትኛውም መልኩ በእኛ በሙስሊሞች የማይደገፍ ተግባር ፣ ባህሪና ስያሜ በመስጠት በየአካባቢው የሚገ  መስጅዶችንም በዚሁ አስተሳሰብ በተጠመቁ ህዝብ በማይፈልጋቸው ጸረ ሰላም፣ ጸረ ሙስሊሞች እጅ እንዲወድቅ በማድረግ ሰላማዊውን ህዝብ ከህዝብ ጋር በማጋጨት የተሳሳቱ መረጃዎችን ለመንግስት በማቀበል ተገቢ ያልሆነ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ሙስሊሙን ህብረተሰብ የሚያስቆጣ ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል።” ሲሉ ገልጠዋል።

“እኛ በአየር ጤና አንሳር መስጅድ አካባቢ የምንገኝ ሙስሊም መእመናን ከእየአቅጣጫው ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየታየ ያለውን ጫና እንቃወማለን” በማለት ሶስት የአቋም መግለጫዎችን አውጥተዋል።

ሙስሊሞቹ ” ከዚህ ቀደም መስጂዳችንን ባካተተ መልኩ የተቋቋመው የሀይማኖቶች ጉባኤ በነበረበት እንዲቀጥል፣ መስጅዳችንን ማግለል እንዲቆም፣ አዲስ የመጣውን ለእስልምናም ይሁን ለአገራችን ደህንነትና ሰላም አደጋ የሆነውን የአህባሽ አስተሳሰብ በማራገብ ይህን ያልተቀበለ ሁሉ አሸባሪ ፣ አክራሪ ማለቱን እንዲያቆምና በአጠቃላይ በአካባቢው እየተከሰተ ያለውን የማዋከብ እንቅስቃሴ እንቃወማለን” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የአህባሽን አስተምህሮ ይቃወማሉ የተባሉ ሙስሊሞች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህን አስተምህሮ ለማስፋፋት ፖሊሲ ቀርጾ በመንቀሳቀስ ላይ ነው። በርካታ በውጭ እና በአገር ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞችም ተቃውሞአቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

በወረታ በቀርቡ አንድ አህባሽን አልቀበልም ያለ ሙስሊም ሲገደል በርካቶችም ታስረዋል። በአድርቃይ ወረዳም እንዲሁም በአስራዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ካለፈው ወር ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ።