የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ወጣ

ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ስምንተኛ ክፍል ያልደረሰ/ች ሠራተኛ ወደውጭ ሀገር መላክ የሚከለክል ሲሆን በሥራው የሚሰማሩ ኤጀንሲዎች ወደ 2 ሚሊየን ብር ወይም 100 ሺ ዶላር ለዋስትና ማስከበሪያ ካላስያዙ ወደስራ እንዳይገቡ ክልከላ አስቀመጠ፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለውን አዋጅቁጥር 632/2001 ሙሉ በሙሉ የሚሰርዘው ይህ ረቂቅ አዋጅ በቀድሞ አዋጅ ፈቃድ የተሰጣቸው ኤጀንሲዎች በአዲሱ አዋጅ መሰረት በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ ፈቃድ እንዲያወጡ ያስገድዳል፡፡
በተለይ ወደአረብ ሀገራት የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ስምንተኛ ክፍል እንዲሆን በተጨማሪም በሚሰማሩበት መስክ ተገቢውን ሰልጠና ወስደው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው በረቂቁ ደንግጎአል፡፡
ሠራተኞችን መላክ የሚቻለው ሀገሪቱ የስራ ስምሪት ስምምነት ወደአላቸው ሀገራት ብቻ ሲሆን ላኪ ኤጀንሲዎች የሚልኩዋቸውን ሠራተኞች ጉዳይ የመከታተል ሙሉ ሃላፊነት እንዳለባቸው ፣ከክፍያና ጉዳት ጋር የተያያዙ አቤቱታዎች
ሲቀርቡ ተጣርተው ኤጀንሲው በዋስትና ካስያዘው ገንዘብ ላይ እየተቀነሰ እንዲከፈል የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊያዝ እንደሚችል ደንግጎል፡፡
አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ አፈጻጸም ከሁለት ዓመት በፊት የታገደ ሲሆን ሌላ የተሻሻለ አዋጅ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ይወጣል ቢባልም ሳይወጣ በመቆየቱ ሕገወጥ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ተንሰራፍቶ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
አዋጁ በቀጣይ ዓመት መጀመሪያ ፓርላማው ያጸድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በአረብ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በአረብ ሃገራት ለሚኖሩት ዜጎቹ ምንም ዓይነት ከለላም ሆነ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንደማይሰጥ ከስደት ተመላሾች ተናግረዋል፡፡
በአረብ ሀገር ረዢም አመታት የኖሩ ከአረብ አገር ተመላሾች እንደተናገሩት በመንግስት እውቅና ህጋዊ ተብለው በኮንትራት የሚሄዱ ወገኖች ከፍተኛ ስቃይ እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል፡፡
ለስራ ከሄዱ በኋላ በአሰሪዎቻቸው በሚደረስባቸው እንግልት በየሃገሩ ለሚገኙ ኢምባሲዎች ደውለው ያለውን ችግር ሲያሳውቁ በጎ ምላሽ እንደማይሰጣቸው ይገልጻሉ፡፡በአንጻሩ ከሌሎች የሩቅ ምስራቅ ሃገራት ሚመጡ ዜጎች መብታቸው በተሻለ መልኩ በየሃገራቸው ኢምባሲዎች ከለላ ሲሰጣቸው ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በህጋዊ መንገድ ለስራ የሄዱት ኢትዮጵያውያን ችግር ሲያጋጥማቸው ለኢምባሲው ሰራተኞች ሲደውሉ ምንም ዓይነት ምላሽ እንደማያገኙ ገልጸው፤ የእርዳታ እጃቸው የሚዘረጋው በኢትዮጵያዊ ዜግነታችን ሳይሆን በዝምድና ፣ በብሄርና በምንናገረው ቋንቋ መሆኑን በየጊዜው በማየት መታዘባቸውን ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵዊ በዜግነቱ አገልግሎት እንደማያገኝ የሚናገሩት ከስደት ተመላሾች በገዢው መንግስት እውቅና በኮንትራት ወደ አረብ ሃገራት የሄዱ ወገኖችም በስቃይ ብዛት እስከ ማበድ ቢደርሱም ኢምባሲው ዘወር ብሎ እንደማያያቸው ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።
ከአመት በፊት ከሳውድ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ዜጎች አብዛኞቹ ተመልሰው መሄዳቸውን መንግስት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።