በምስራቅ ጎጃም ዞን ከምርጫ ጋር በተያያዘ አርሶ አድሮች እየታሰሩ ነው

ኢሳት ዜና (ሰኔ 26 2007)

በቅርቡ በምስራቅ ጎጃም ዞን በወጣት እጩ የፓርላማ ተወዳዳሪ ላይ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በርካታ ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው በመታሰር ላይ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጡ ።
በዞኑ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከ 15 አምት በፊት ያልከፈላቹት የማዳበሪያ እዳ አለባችሁ እየተባሉ በጅምላ መታሰራቸውን የተናገሩት እማኞች ገበሬዎቹ በሞት የተላዩዋቸውን ዘመዶች እዳ ጭምር እንዲከፍሉ መገደዳቸውም ታውቋል።
የዞኑ ባለስልጣናት የማዳበሪያ እዳን ምክንያት ቢያድርጉም አርሶ አደሮቹ ለእስር የተዳረጉት ባለፈው ወር በተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ ያላቸው የፖለቲካ አመለካከት ታይቶ እንደሆነ ነዋሪዎች አስረድተዋል ።
ከሳምንት በፊት በዞኑ የተከፈተው የጅምላ እስር ዘመቻም ሰሞኑን በአዲስ መልክ ቀጥሎ እንደሚገኝ የሚናገሩት እማኞች በተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት ላይም ከፍተኛ ማዋከብ እየተፈጸመ እንደሆነ ገልጸዋል።
በቅርቡ በዞኑ የፓርላማ እጩ ተወዳዳሪ የነበረው የወጣት ሳሙኤል አወቀ መገደልን ተከትሎ በአካባቢው የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት “እንገላችኋለን” የሚል ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው እንደሆነም ከሀገር ቤት የተገኘው መረጃ አመልክቷል።
ኢሃዴግን ይቃወማሉ የሚል ዛቻ የደረሰባቸው የዞኑ ነዋሪ የሆኑት ቄስ ዋልተንጉስ ለደህንነታቸው በመስጋት ለአካባቢው ከነቤተሰብ አባሎቻቸው መሰደዳቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት ነዋሪዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን በሚገኙት ሁሉም ቀበሌዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከዞኑ ባለስልጣናት ምላሽን ለማግኘት የተደረገ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።