ሜሮን አለማየሁ ተፈረደባት!

ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ሰበብ ታስራ ‹‹ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ በማወክ›› ወንጀል የተከሰሰችው ሜሮን አለማየሁ የ6 ወር እስር ተፈርዶባታል፡፡ ሜሮን አለማየሁ ሚያዝያ 14 በተጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ወያኔ ሌባ፣ መንግስት የለም፣ አትነሳም ወይ፣ የታረደው ወገን ያነተ አይደለም ወይ›› በሚል ሁከትና ብጥብጥ ፈጥራለች ተብላ በተከሰሰችበት ክስ ፣ በዋስ ወጥታ ጉዳዩን ስትከታተል የቆየች ሲሆን ሰኔ 26/2007 ዓ.ም በጎፋ ፍርድ ቤት ቀርባ 6 ወር ተፈርዶባታል፡፡
አቃቤ ህግ በክሱ ሜሮን አለማየሁ ድንጋይ እንደወረወረች ቢጠቅስም፣ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ስትወረውር አላየንም ብለው መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግ ሜሮን ከ200-300 የሚሆኑ ሰዎችን በመምራት ሁከትና ብጥብጥ እንደፈጠረች ጭብጥ ቢያስይዝም፣ ምስክሮቹ አቃቤ ህግ እንዳለው ሳይሆን ሜሮን አለማየሁን ከ20-30 ከሚሆኑ ሰዎች ጋር እንዳዩዋት መስክረዋል፡፡ በተመሳሳይ አቃቤ ህግ ሜሮን አለማየሁ ብጥብጡን የፈጠረችው መስቀል አደባባይ ላይ ነው ሲል፣ ምስክሮቹ አቃቤ ህግ ባለው ሰዓት ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው መንገድ እንዳዩዋት መስክረዋል፡፡
አቃቤ ህግ ሜሮን አለማየሁ ብጥብጡን የፈጠረችው ከ3 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ባለው ጊዜ ነው ያለ ሲሆን፣ የሜሮን አለማየሁ የመከላከያ ምስክሮች ከ3፡20 እስከ 5 ሰዓት ከእሷ ጋር አምባሳደር አካባቢ እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቱ ምስክሮቹ ከ3፡20 በፊት የት እንደነበረች አላስረዱም እንዲሁም ሻሂ ቤት ውስጥ የጠጡትን ለስላሳ አልገለጹም በሚል ምስክርነቱን ውድቅ አድርጌዋለሁ በሚል መፍረዱን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግባል