የኢትዮጵያ የውጪ ዕዳ 200 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተመለከተ

ጥቅምት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከኢትዮጵያ የገንዘብና የ ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው 134 ቢሊዮን ብር የነበረው የ አገሪቱ የውጪ ዕዳ እጅግ በሚያስደነግጥ መልኩ ባለፈው ሰኔ ወር ወደ 200 ቢሊዮን ብር አሻቅቧል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዶክመንንት ከዚህም በተጨማሪ የመንግስት የ አገር ውስጥ ብድርና ዕዳ 60 ቢሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል።

ይህ ዕዳ ፤ኢትዮጵያ በቅርቡ  ለባቡር ሀዲድ መስመር ግንባታ በሚል ከቻይና የተበደረችውን 3 ቢሊዮን ዶላር ወይም ሀምሳ ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከኤክሲም ባንክ የተበደረችውን 300 ሚሊዮን ዶላር አያካትትም።

አገሪቱ በቅርቡ የተበደረችው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲጨመር የውጪ ዕዳው ከተጠቀሰው አሀዝ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ኤክስፐርቶቹ ገልጸዋል።

ከዕዳው ውስጥ 85 ቢሊዮን ብሩ  <<መልቲላተራል ክሬዲተርስ>>(አበዳሪዎች) ከሚባሉት ከአይ.ኤም. ኤፍ፣ ከወርልድ ባንክና ከ አፍሪካ ልማት ባንክ የተገኘ ብድር ሲሆን፤49 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ ከቻይና፣ ከህንድ፣ከኩዌትና ከ ኤግዚም ባንክ በሁለታዮሽ ግንኙነት የተገኘ ብድር ነው።

የብድሩ መጠን እያሸቀበ በሄደ ቁጥር አገሪቱ በየዓመቱ የምትከፍለው የወለድ መጠን እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክተው የሚኒስቴሩ ዶክመንት፤በዚህ ዓመት ብቻ ለ 134 ቢሊዮን ብር የብድር ዕዳ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ወለድ እንደሚከፈል ይገልጻል።

አገሪቱ በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ በተዘፈቀችበት ጊዜ ከአቅም በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶችን  ለመስራት የሚደረገው የብድር ሩጫ አሁንም አለመቆሙ የ አገሪቱን ኢኮኖመ ክፉኛ እያናጋው እንደሆነ ያስረዱት የመስሪያ ቤቱ ኤክስፐርት፤ለመጪው ትውልድ ዕዳና ባርነት አውርሶ ለማለፍ የሚደረገው ሩጫ ይህች አገር ፤ለትውልድ ሀላፊነት በማይሰማቸው ሰውች መዳፍ ስር መውደቋን ሚያመላክት ነው ብለዋል።

ያለፉትን ሦስት ዓመታት ሳይጨምር ኢትዮጵያ በዘመነ-ኢህአዴግ በእርዳታና በብድር ካገኘችው ገንዘብ ውስጥ ወደ 12 ቢሊዮን ዶላር ወይም አሁን ኢትዮጵያ ካለባት የውጪ ዕዳ የሚበልጥ ገንዘብ በከፍተኛ ባለስልጣናት፣በዘመዶቻቸውና በነጋዴ ጓደኞቻቸው ስም በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ወጥቶ በውጪ አገር ባንኮች እንደተቀመጠ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ማጋለጡ አይዘነጋም።