ቻይና አፍሪካውያን ዲሞክራሲን ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታግዝ አስታወቀች

ጥቅምት ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ሃላፊ የሆኑት ሚስተር ሉ ሻየ ይህን የተናገሩት በአፍሪካ እና በቻይና ምሁራን መካከል በኢትዮጵያ በደብረዘይት ከተማ በመካሄድ ላይ ባለው ጉባኤ ላይ ነው።

ባለስልጣኑ እንዳሉት ቻይና አፍሪካዊያን ዲሞክራሲን ብቻ ሳይሆን፣ የህግ ተቋማትን ለመገንባት የሚያደርጉትን ጥረት ታግዛለች። አገራቸው በመልካም አስተዳዳር ላይ ያላትን ልምድ ለአፍሪካ አገሮች ለማካፈል ዝግጁ መሆኑዋንም ገልጠዋል።

አንዳንድ ሰዎች ቻይና ከአፍሪካ የኢኮኖሚ ጥቅም ብቻ ለማግኘት እንደምትፈልግ የሚገልጹት ትክክል አለመሆኑን ባለስልጣኑ በመግለጽ፣ ቻይና በአገሮች ጉዳይ ጣልቃ አትገባም የሚለው አመለካከት፣ ቻይና ስለ አፍሪካ ጸጥታ እና ሰላም  ምንም አይመለከታትም ተብሎ እንዳይተረጎም አሳስበዋል።

ቻይና ለአፍሪካ ትላቁዋ የንግድ ሸሪክ መሆኑዋንና ለአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሀይል በማዋጣት ረገድም መሪ መሆኑዋን ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር የሆኑት አቶ ደመቀ መኮንን፣ የቻይናና የአፍሪካ ምሁራን ስለመልካም አስተዳዳር፣ ሰላምና ጸጥታ በግልጽ በመወያየት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ምእራባዊያን ቻይና በአፍሪካ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዳይስፋፋና መልካም አስተዳደር እንዳይስፋፋ እና ሰብአዊ መብቶች እንዳይከበሩ እንቅፋት ሆናለች በማለት ይከሳሉ። በሌላ በኩል ቻይና ምእራባዊያን በሰው አገር ጉዳይ ጠልቃ ይገባሉ በማለት ትከሳለች።

በርካታ  የአፍሪካ መንግስታት ከምእራባዊያን የሚሰነዘርባቸውን ተቃውሞ ለመሸሽ ቻይናን እንደመጠጊያ እየተጠቀሙባት መሆኑ ይታወቃል።