የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አባቶች ለቤተክርስቲያኗ መከፋፈል መንግስትን ተጠያቂ አደረጉ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 11 ቀን 2010 ዓ/ም ) ዘጋቢያችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራት ኅብረት በቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ስለሚካሄደው እርቀ ሰላምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ ሲኖዶሱ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ በሀገር ውስጥ ሲኖዶስ ቅርብ ክትትል የሚያደርጉ የስራ ኃላፊዎችን አናግሮ ባጠናቀረው ዘገባ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከእርቅ ሰላሙ ጋር ዳግም የጠላችውን መንገድ እንዳትመለስበት ፖለቲካዊ ጫናዎችን እና አለመግባባቶችን በግልፅ ለምዕምናን ይፋ አድርጋ ልትፈታ ይገባል ብለዋል፡፡
በግልፅ የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ኢህአዴግ ኦርቶዶክስን የማዳከም አቋም እና ስደተኛው ሲኖዶስ እንዲፈጠር ማድረጉን የመሰከሩበት በመሆኑ፣ በምዕምናን መካከል በተፈጠረው የመረጃ ውዥንብር እና ስርዓቱ በቤተ ከርስቲያኒቱ ላይ ላደረሰው በደል ይቅርታ መጠየቅን ያካተተ ውሳኔ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡
አባቶች እንደሚናገሩት፣ “ኢህአዴግ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ስልጣን ላይ ሲወጣ በደርግ ዘመነ መንግስት ፓትርያርክ የነበሩት አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር የተባረሩት በራሱ በኢህአዴግ የወቅቱ አመራሮች በመሆኑ እና ሰርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጥሰው ለሃይማኖቷ ‘የለም ሹመቱ አይገባንም’ ሊሉ ሲገባ፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለማጥቃት ካሰፈሰፈው ቡድን ጋር በማበር የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ፓትርያርክነት ስልጠና የተቀበሉ ፣ ጥብቅና ለቤተክርስቲያን ያልቆሙ አባቶች እንዲፈጠሩ ሁኗል፡፡
አቡነ ጳውሎስ በዚህ ክፍተት ወደ ስልጣን መምጣታቸውንና በሀገር አንድነት ላይ እንዳትቆም በማዳከሙ ስራ በሯ የሚከፈትበት መንገድ እንደተፈጠረ የገለጹት አባቶች፣ በኢህአዴግ ስርዓት በነበረው ክፉ አመለካከት ቤተ-ክርስትያኒቱ በውጪያዊ ጫና እና በውስጣዊ ችግሮች ተተብትባ እንድትቆይ አድርጓታል ብለዋል፡፡ የጳጳሳት ፀብ፣ የቀሳውስት አቤቱታ፣ የምዕመናን አያሌ ጥያቄዎች፣ የገንዘብ እና የውስጥ አስተደደሮች በማኅበረ ቅዱሳኖች ላይ የሚደረገው ጫና ሁሉ በጉልህ የታዩ ችግሮች ነበሩ ሲሉ ያነሳሉ።
በሁለቱ ሲኖዶስ መካከል እና በምዕመናኑ የተፈጠረው ግራ መጋባት የጠራ ፣ ፖለቲካውም የድርሻውን ሃላፊነት የሚወስድበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡ አባቶች አሁን ያለው ግራ መጋባት እና ብዥታ እንዲጠራ ቅድመ ውይይቱ ከአቋም መግለጫ ባለፈ ለምዕመናን እና ለሚዲያዎች ክፍት ሊሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ድፍን እርቀ ሰላም ያሉት አባቶች፣ አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር እንዲወጡ ከሀገረ ያሰገደዳቸው ራሱ ኢህአዴግ በመሆኑ በእያንዳንዱ አሰራር ኃላፊነቱን ከመወሰድ ጀምሮ ፣ ለተፈጠረው ሁለት የተፈረካከሰ ሲኖዶስ ተጠያቂነቱ ግልፅ ሁኖ መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡
“አቡነ መርቆርዮስ ከሀገር ለምን ወጡ ሲባሉ፣ “ለደህንነቴ በመስጋት ነው” ብለዋል የሚለው አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ መሆኑን የገለጹት አባቶች፣ “አንድ የሃይማኖት መሪ፣ የራሱን ደህንነት ለመጠበቅ ሃይማኖቱንና ህዝቡን ጥሎ ይሄዳል? የፈለገ የደህንነት ስጋት ቢኖርስ? ለእግዚአብሔር ማደር? ስጋትን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ሰጥቶ የመጣውን ሁሉ በፅናት መቀበልስ እንዴት አልቻሉም? በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉን” ሲሉ የሲኖዶሱ አባቶች ይናገራሉ። ይህ በግልፅ መግለጫ ሊሰጥበት ይገባል የሚሉት አባቶች፣ አቡነ መርቆርዮስ ሀገርን እና ሕዝብን ጥሎ በመሄድ የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ያደረጋቸውን ምክንያት ከ60 ሚልየን ምዕመን በላይ ተከታይ ያላት ቤተ ክርስቲያን ማወቅ ትፈልጋለች ብለዋል።
ሲኖዶሱ ከመግለጫው በፊት ባደረገው ምክክር ያነሳቸው አንኳር ጥያቄዎች ቤተ-ክርስትያኒቱ ከ60 ሚሊዮን በላይ ምዕመናን ይዛ እንዴት በፓርላማ ውስጥ እንኳን አትወከልም ሲል ተነጋግሯል። እርግጥ ነው በሀገሪቱ ውስጥ በሃይማኖት ስም በፖለቲካ መደራጀት አይቻልም። የሚሉት አባቶች፣ ይሁን እንጂ በፓርላማ ውስጥ የድምፅ ውክልና ቢኖር በልዩ ልዩ የፓርላማው ውሳኔዎች ላይ ድምጿ ይሰማ ነበር። ኦርቶዶክስ የስልሳ ሚሊዮን ምዕምኗን ድምፅ ለማሰማት ጥያቄ መጠየቅ አለባት ሲሉ አሰተያየታቸውን ሰጠዋል።
እንደ ቫቲካን የራሳችንን እድል የመወሰን አማራጭ ሁሉ አለን የሚሉት አባቶች ፣ በፓርላማ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ወንበር፣ የቤተ-እምነቶች ወንበር፣ የሴት መብት ተከራካሪ ቡድኖች ወንበር፣ የአካል ጉዳተኞችና ድኩማን የውክልና ወንበር ወዘተ ቢኖር ከየአቅጣጫው ድምጾች ይሰማሉ ይህ ግን አልተተገበረም ብለዋል። እነዚህ ድምጾች እንደማንኛውም የፓርላማ አባል ተወዳድረው አሸንፈው የሚመጡ ሳይሆን መንግስት በራሱ ፍላጐት የሚደለድላቸው ነው። ፓርላማው ውሣኔ ሲያሳልፍም ድምፃቸው ይቆጠራል። ሀገራችን ወደፊት ይህን አሰራር እንድትትገብረው እና ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ሌላው የድምፅ ውክልና ይዞ በመግባት በሀገር ጉዳይ ሊሳተፍ ይገባል ብለዋል፡፡