በሀገር ቤት የሚገኘው ሲኖዶስ ኮሚቴ አባላት ተሸኙ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 11/2010) በሀገር ቤትና በውጭ የሚገኘውን ሲኖዶስ ወደ አንድነት ለማምጣት በሀገር ቤት የሚገኘውና ወደ አሜሪካ የሚያቀናው ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶሱና በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ  አሸኛኘት ተደረገለት።

ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስ ወደ አሜሪካ ላቀኑት አባቶችም አባቶቻችንን ይዛችሁ ኑ መነጋገር ያለብንን ነገር በቤታችን እንነጋገራለን የሚል መልዕክት ማስተላለፈቻውም ተሰምቷል።

በዋሽንግተን ዲሲ የሚካሄደው የአባቶቹ ውይይትም ከሐምሌ 12 እስከ ሐምሌ 21/2010 እንደሚካሄድ ታውቋል።

ሁለቱን ሲኖዶሶች አንድ ለማድረግ በሀገር ውስጥና በውጪ በሚኖሩ የኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ጥረት ሲደረጉ መቆየታቸው ይነገራል።

ከዚህ በፊት ያልተሳኩ ነገር ግን ከፍተኛ መቀራረብ የታየባቸው ግኑኝነቶችም  ተደርገዋል።

ጥረቱ አሁንም ቀጥሎ ባለፈው አንድ ዓመት ከስምንት ወር በሁለቱም በኩል የተዋቀረው ኮሚቴ አባቶቹን ለማገናኘት መንገድ ሲጠርግ መቆየቱንም ነው ከቤተክርስቲያኒቱ የወጣው መረጃ የሚያመለክተው።

የፊታችን ሐምሌ 12 የሚጀመረውና እስከ ሐምሌ 21/2010 የሚቆየው የአባቶቹ ግኑኝነትም ከተኬደው ርቀት አኳያ ውጤታም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚሁ የእርቅ ውይይት ላይ የሚሳተፈው የአዲስ አበባው ኮሚቴ ወደ ዋሽንግተን ለሚያደረገው ጉዞም በሀገር ቤት የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ አሸኛኝት አድርጎለታል ።

የኮሚቴው የሕዝብ ግኑኝነት ሃላፊ አቶ ብርሃን ተድላ ለኢሳት እንደተናገሩት ለአባቶቹ የተደረገላቸው አሸኛኘትና ምኞች ከፍተኛ ነው።

ፓትሪያሪክ አቡነ ማትያስም አባቶቹን ሲሸኙ አባቶቻችንን ይዛችሁ ኑ መነጋገር ያለብንን ነገር በቤታችን  እንነጋገራለን ማለታቸውንም ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

በአሸኛኘት ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም መልካም ምኞታቸውን ለአባቶቹ ማስተላለፋቸውንም ተናግረዋል።

በተያያዘም የኮሚቴ አባላቱ ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር መገናኘታቸውም ታውቋል።

ለአባቶቹ እርቀ ሰላሙ ውጤታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ለእርቀ ሰላሙ ውጤታማነትም መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ እንዲሁም  አባቶች ችግሮቻቸው በሀገራቸውና በቤታቸው ይፈቱ ዘንድ ምኞታቸውን መግለጻቸውን  አቶ ብርሃን ተድላ ገልጸዋል።

የቤተክርስተያኒቱ ምእመናንም ሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድነት እንዲመጡ ያላቸውን መልካም ምኞት በመግለጽ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኮሚቴው የህዝብ ግኑኝነት አላፊ አቶ ብርሀን ተድላ  ምዕመኑ የሁለቱ ሲኖዶሶች ወደ አንድነት መምጣት በቤተክርስቲያኗ ሞገስ ላይ ሌላ ሞገስ መጨመር ነው እያለ ውጤቱን  በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቀ ነው ማለታቸውን ገለጸዋል።

ባለፉት 25 ዓመታት የቤተክርስትያኒቱ አባቶች የሀገር ውስጥና የውጪው ሲኖዶስ በሚል ተከፍሎ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በውጪ የሚገኘው ሲኖዶስ ቀኖና ተጥሷል በሚል ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።

ሁለቱ ሲኖዶሶች ለእርቅ በሚነቀሳቀሱበት ሰዓት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ  ቀኖናውን ለማስተካከል መልካም አጋጣሚ ነው በሚል እንቅስቃሴ  ቢደረግም በሕወሃት አመራሮች ጣልቃ ገብነት ሳይሳካ መቅረቱ የሚታወስ ነው ።