ቤተ-ክርስቲያኒቱ ዳግማዊ ምኒልክ ፊት ለፊት በሚገኘው በተለምዶ ‹‹ጠጠር ሕንፃ›› በሚባለው ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ግንባታዎቿ ሕገወጥ እየተባሉ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን አጥብቃ ተቃወመች::
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር መሰንበቻውን በቤተክህነት ሕንፃ ላይ ባካሄደው ዘመቻ፤ አምስት የንግድ ቤቶችንና መጋዘኖችን
አፍርሷል:: እንደ ሪፖርተር ዘገባ፤ ከቤተክህነት ቤቶቹንና መጋዘኖቹን ተከራይተው ይሠሩ የነበሩ ነጋዴዎች ወረዳው የወሰደውን ዕርምጃ ሕጋዊነት የሌለው ሲሉ ከቤተክህነት ጋር በመሆን እየተቃወሙት ይገኛሉ::
ተቃውሞ በማሰማት ላይ የሚገኙት ድርጅቶችም፦ ሐረግ ካፌ፣ ዳሸን ምግብ ቤት፣ አዲስ ቢዝነስ ዩኒቲ፣ ፈቃዱ ፋንታዬ የጽሕፈት መሣርያ መደብርና
ዩኒቨርሳል ቤተ መጻሕፍት ናቸው:: እነዚህ የንግድ ሥራዎች የሚካሄዱባቸው ግንባታዎች “ሕገወጥ ግንባታዎች ናቸው” በሚል ነው ወረዳው ዕርምጃውን የወሰደው::
በተወሰደው እርምጃ ግራ የተጋቡ በህንፃው ውስጥ የሚሰሩ ነጋዴዎች፦ “ሕገወጥ ማለት ምንድን ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ:: ቤተክህነት በደርግ መንግሥት የተወረሱባትን ሕንፃዎች በ አቶ መለስ ዜናዊ ፊርማ በ1998 ዓ.ም. መልሳ ማግኘቷ ይታወሳል::
ቤተክህነት በ አቶ መለስ ፊርማ ከተረከበቻቸው ሕንፃዎች መካከል አንዱ ‹‹ጠጠር ሕንፃ›› ሲሆን፣ ከዚሁ ሕንፃ ጋር አሁን በወረዳው ሕገወጥ የተባሉ ግንባታዎችንም አብራ መረከቧን ሠራተኞቿ ይገልጻሉ::
በህንፃዎቹ እየሠሩ ያሉ የንግድ ሰዎች ከቤተክህነት ጋር ሁከት ይወገድልኝ ሲሉ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር:: ይሁንና ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ፣ ወረዳው -የክስ ምክንያት የሆኑት ግንባታዎች እንዲስተካከሉ መጠየቁና ማሸጉ፤ የተሰጠውን የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት መወጣት እንጂ ሁከት መፍጠር አይደለም ሲል ወስኗል::
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት የሕግ ባለሙያ ሊቀ ጉባዔ ቀለመወርቅ
ውብነህ ፦”የአስተዳደሩ ፍርድ ቤት በክፍለ ከተማና በወረዳ ሥር ያለ ፍርድ ቤት ነው:: መሐንዲሶቹም በዚሁ መዋቅር ውስጥ ያሉ ናቸው:: ገለልተኛ አይደሉም:: ሁሉም ፤አንድ አካል ናቸው ፤ ገለልተኛ አካል ቢሆኑ፤ ግንባታው ሕገ-ወጥ እንዳልሆነ ዓይን አይቶ ልብ ይፈርዳል፤››ሲሉ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍርደ-ገምድል ውሳኔ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል::
በምርጫ 97 ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ የ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን፦”የነፍጠኞች መሸሸጊያ ዋሻ ሆኗል ”በማለት መናገራቸው አይዘነጋም።