የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሥራቸውን ለቀቁ

ሰኔ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ላለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትን በዋና ሥራ አስፈጻሚነትና በቢሮ ኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ሽፈራው ዓለሙ፣ ሥራቸውን ከሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራቸውን   መልቀቃቸው ተዘገበ።

አንዳንድ ወገኖች ሥራ አስኪያጁ  ሥራቸውን የለቀቁት ከጤና ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፈቃዳቸው ነው ሲሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ የሙስና ክስ ስለተመሰረተባቸው ሥራቸውን ይለቁ ዘንድ ከመንግስት ባለስልጣናት ጫና ተደርጎባቸው ነው ይላሉ።

የሪፖርተር ምንጮች  ሥራ አስኪያጁ  አቶ ሽፈራው ከፍተኛ የሆነ የስኳር ሕመም ስላለባቸው  በተደጋጋሚ ለትራንስፖርት ሚኒስትሩ የመልቀቂያ  ጥያቄ ሲያቀርቡ መክረማቸውን አውስተዋል፡፡

እንደ ምንጮቹ ገለጻ፣ አቶ ሽፈራው ሕመማቸው እየጠነከረ በመምጣቱ ሰኔ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚኒስትሩ ያስገቡት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ተቀባይነት በማግኘቱ ሥራቸውን ለቀዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ሙያቸው ምህንድስና መሆኑን የገለጹት የጋዜጣው ምንጮች፣ መንግሥት በሙያቸው በማንኛውም ኃላፊነት ቢመድባቸው ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆኑ መናገራቸውን  ገልጸዋል፡፡

ከጤና ጋር በተያያዘ ሥራቸውን ለመልቀቅ እንደተገደዱ የገለጹት ምንጮች፤ አቶ ሽፈራው በሙያቸው በማናቸውም ቦታ ለመስራት ዝግጁ ናቸው ማለታቸው፤ በእርግጥ ሥራቸውን የለቀቁት በፈቃዳቸው ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

በአቶ ሽፈራው ሥራ መልቀቅ ዙሪያ  ለጋዜጣው አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖች ፣ አቶ ሽፈራው ሥራቸውን ለመልቀቅ የተገደዱት ከዓመት በፊት ከሙስና ወንጀል ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው ክስ ስለተመሠረተባቸው፣ ምናልባት ሥራቸውን ለቀው የክርክሩን ውጤት እንዲጠባበቁ ከባለሥልጣናት ጫና ተደርጐባቸው ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ምህንድስና የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላ፣ በኢንፍራስትራክቸር ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከጃፓን አገር አግኝተዋል፡፡

ለስምንት ዓመታት በኤርፖርቶች ድርጅት ከመሥራታቸውም በተጨማሪ፣ በቀድሞው በኢኮኖሚና ልማት ሚኒስቴር በተለያዩ ኃላፊነቶች እና ወደ ሁዋላ ላይም በሚኒስቴሩ- የመሠረተ ልማት መምርያ ሥራ አስኪያጅ ሆነው አጠቃላይ ከ25 ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡

የአቶ ሽፈራው ዓለሙ  ሥራቸውን እንዴት በፈቃዳቸው ሊለቁ እንደቻሉ ለቀረበላቸው ጥያቄ፦በሕመም ምክንያት በራሴ ፈቃድ ለቅቄያለሁ፤ ከማለት ውጭ ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠባቸውን ጋዜጣው ጠቁሟል፡፡