ፕሬዚዳንት ግርማ ከሊቀ ትጉሐን አስታጥቄ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው ተባለ

ሰኔ ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በከባድ የማታለል ወንጀል የተከሰሱት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኀበር
ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊቀትጉሃን አስታጥቄ አባተ የቀረበባቸው ክስ እንዲቋረጥ ለፍትህ ሚኒስትር ደብዳቤ እስከመጻፍ
የደረሱት ከሊቀመንበሩ ጋር የቅርብ ትስስር ስለነበራቸው እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ  በፖሊስ ተይዘው ችሎት የቀረቡት የ82 ዓመቱ አዛውንት ሊቀትጉሃን አስታጥቄ አባተ በከባድ
የማጭበርበር ወንጀል የተከሰሱት የቀድሞ የአዲስአበባ ከንቲባ አቶ አርከበ ዕቁባይ ለደሃ አርበኞች መርጃ የሰጡትን
የኮንዶሚየም ቤቶች ለማይገባቸው ሰዎች በማስተላለፋቸውና ራሳቸውም የግል መኖሪያ ቤት እያላቸው እንደሌላቸው
አጭበርብረው ቤት በመረከባቸው ነው፡፡

ሊቀ ትጉሃን አስታጥቄ አባተ ከፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስና ከቀድሞ የኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ
ፓትያርክ አቡነ ጳውሎስ ጋር ቅርርብ እንደነበራቸው፣በተለይም  ከደሃ አርበኞች ስም ባሰባሰቡት
ገንዘብ የተለያዩ የምግብና የመጠጥ ግብዣዎችን  ወደቤተመንግስት በተደጋጋሚ ይልኩ እንደነበር ታውቋል፡፡

ሊቀ ትጉሐን አስታጥቄ  በፕሬዚዳንቱ ስም ሰዎችን እስከማስፈራራት ይሄዱ እንደነበር፣ ክስ ሲመሰረትባቸውም

እንዲያማልዱአቸው እንደተማጸኑዋቸውና ፕሬዚዳንቱም በድፍረት የሙስናና ብልሹ አሰራር ክስ ይቋረጥ ብለው ደብዳቤ እስከመጻፍ መሄዳቸው ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ ደብዳቤውን ከመጻፋቸው በፊት ለስማቸው ጥሩ እንዳልሆነ የሚገልጽ ምክር ከአንዳንድ አባት አርበኞች ቀደም ሲል ተለግሶአቸው እንደነበር የጠቀሱት ምንጮቻችን በማህበሩ አመራሮች መካከል ተፈጠረ የተባለውን ችግር በተመለከተ በማያገባቸው ጉዳይ ገብተው በቤተመንግስት ስብሰባ በመጥራት ከሊቀትጉሃን አስታጥቄ ጎን በመቆም አጋርነታቸውን እስከማሳየት ደርሰው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አርከበ ዕቁባይ ለጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር
አባላት ለሆኑና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች የሰጡትን የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሸጠው ለግል ጥቅማቸው አውለዋል
በሚል የተጠረጠሩት የማህበሩ ፕሬዚዳንትና አንደኛ ተከሳሽ ሊቀትጉሃን አስታጥቄ አባተ ፣ የማህበሩ ዋና ጸሐፊ
አስር አለቃ ሰጥአርጌ አያሌው እና የማኀበሩ የአስተዳደር ኃላፊ አቶ በቀለ ሻረው በከባድ ወንጀል ክስ
ተመስርቶባቸው በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት አምስተኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው እየታየ ሲሆን ፍ/ቤቱ የክስ ዝርዝሩን
ለመስማትና የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለሐምሌ 4/2005 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል፡፡