የኢትዮጵያ ኤምባሲ መግለጫ አቅጣጫ ለማሳት ያለመ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 17/2010) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀል ግድያ ላይ ያወጣው መግለጫ ጉዳዮን አቅጣጫ ለማሳት የታለመ በመሆኑ እንደሚያወግዘው በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ገለፀ::

የኮሚኒቲው ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ ለኢሳት እንደገለፁት የኤምባሲው መግለጫ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ እንደመጮህ የሚቆጠር ነው::

ኮሚኒቲው ይህን ያለው የአክቲቪስት ገዛህኝ ገብረመስቀልን ግድያ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ተገቢ አይደልም በሚል በፕሪቶሪያ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ  ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ነው ።

መግለጫው በሀዘን ላይ ላለው ኮሚኒቲያችን ተጨማሪ ሀዘን የሚፈጥር ነው ብሎታል ኮሚኒቲው::

የገዛህኝ ነብሮን መገደል በተመለከተም የቀድሞ የኢትዮጵያ የሃገር መከላከያና ፖሊስ     ሰራዊት ማህበር ባወጣው መግለጫ የነጻነት ታጋዮችን በማፈንና በመግደል የነጻነት ትግሉን መቀልበስ አይቻልም ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በኤምባሲው መግለጫ ቁጣውን እየገለጸ ነው።

ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ላይ አሰቃቂ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸሙ ተንፍሶ የማያውቀው በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልተለመደ ሁኔታ የወንድማችንን ግድያ ለማውገዝ መግለጫ ማውጣቱ ጉዳዩን በጥልቀት እንዲታይ የሚያደርግ ነው ብሏል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰኞ ባወጣውና በማህበራዊ ድረገጹ ጭምር ባሰራጨው መግለጫ በገዛህኝ ገብረመስቀል ሞት መደንገጡንና ማዘኑን ይገልጻል።

ለቤተሰቦቹም መጽናናትን የሚመኘው ይህ መግለጫ ከግድያው ጋር በተያያዘ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ የራሱን ጥረት እንደሚያደርግም ያስረዳል።

የኤምባሲውን መግለጫ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ከተጠያቂነት ለመሸሽና ጉዳዩን ለማድበስበስ ካልሆነ በቀር የሚፈይደው ምንም ነገር የለም ሲል በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ለኢሳት ገልጿል።

ምንም እንኳን ጉዳዩ በፖሊስ እጅ የተያዘና ምርመራ እየተካሄደበት ቢሆንም በህወሀት አገዛዝ አማካኝነት በቅጠረኛ ገዳዮች እጅ ለመፈጸሙ ምልክቶች እንዳሉ ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊው የመብት ተሟጋች ገዛህኝ ገብረመስቀል ነብሮ ባለፈው ቅዳሜ በአንድ ምግብ ቤት ደጃፍ ባልታወቀ ሰው በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

ገዛህኝ ግድያው ከተፈጸመበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በነበረ ዝግጅት ላይ እንዳይገባ የተደረገበትን ክልከላ ጥሶ በመግባቱ በወቅቱ ዛቻ እንደደረሰበት በስፍራው የነበሩ እማኞች ገልጸዋል።

በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/የሚመራው የኢትዮጵያ የደህንነት መስሪያ ቤት በየሀገሩ ኤምባሲዎች በተለይም በጎረቤት ሃገራት አፋኝና ገዳይ የቡድን አባላትን በወታደራዊ አታሼ እንደሚያሰማራ ሲገልጽ ቆይቷል።

በዚህ ረገድ ሟቹ አቶ ክንፈ ገብረመድህን በመሩት ዘመቻ የቦረናው ተወላጅና የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ምሩቅ የነበሩት ሻለቃ ጃተኒ አሊ በሌላ ስማቸው መባጺዮን አሊ በናይሮቢ በአንድ ሆቴል ውስጥ መገደላቸው ይታወቃል።

አሁን ዘግይተው የሚወጡ ሪፖርቶች የሻለቃ ጃተኒ አሊ ግድያ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር  በነበሩት በአቶ ስዬ አብርሃ የተመራ መሆኑን ይገልጻሉ።

በዚህ መልክ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጎረቤት ሀገራት ሲገደሉ ብዙዎችም ታፍነው ወህኒ ቤት ገብተዋል።

ታፍነው ወህኒ ቤት ከገቡት ውስጥ ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ ወህኒ ቤት ማረፉ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ፕሪቶሪያ ላይ የተገደለውን ገዛህኝ ገብረመስቀልን ገዳይ አፈላልጎ ለመያዝና በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ምርመራ ለማድረግ የግል መርማሪዎችን ለመቅጠር እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ይህንን የምርመራ ወጪ ለመሸፈንና ቤተሰቡን ለመደገፍ በጎፈንድ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ትላንት ተጀምሯል።

በግሎባል አሊያንስ አማካኝነት እየተሰበሰበ ያለው ገንዘብ ግቡ 50ሺ የአሜሪካን ዶላር ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 1 ሺ 9 መቶ የአሜሪካን ዶላር ተሰብስቧል።

በተያያዘ ዜና በትውልድ አካባቢው አዲስ አበባ ኮሪያ ሰፈር የሻማ ማብራት ስነ ስርአት ተካሂዷል።

በፕሮግራሙ ላይ ጓደኞቹና ወዳጆቹ እንዲሁም የሰፈሩ ልጆች የገዛህኝ ገብረመስቀል ምስል ያለበትን ቲሸርት በመልበስ አስበውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያና ፖሊስ ሰራዊት ማህበር የአባላችን ግድያ ከነጻነት ጉዞው የሚያስቆመን አይደለም ሲል መግለጫ አውጥቷል።

ጓዳችንን በዚህ መልኩ ብናጣውም ይዞ የዘለቀውን የነጻነት ዓርማ ከዳር ሳናደርስ ለአፍታም አናቀላፋም ሲል ማህበሩ አስታውቋል።

ለቀብር ስነስርዓቱ አንድ ተወካዩን ከሰሜን አሜሪካ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚልክም ማህበሩ ገልጿል።

የአክቲቪስት ገዛህኝ ነብሮ የቀብር ስነስርአትም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የፊታችን ቅዳሜ ይፈጸማል።