በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ተጠርጣሪዎችን በነጻ ያሰናበቱት ዳኛ ታሰሩ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 17/2010) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በኮማንድ ፖስት የተያዙ ተጠርጣሪዎችን በነጻ አሰናብተዋል የተባሉ ዳኛ መታሰራቸው ተሰማ።

ዳኛው በሰጡት ውሳኔ ላይ የለመታሰር መብታቸው ተጥሶ ወደ ወህኒ መውረዳቸውም ታውቋል።

ዳኛው ለሚመሩት ችሎት ተጠርጣሪዎቹን አቅርበዋል የተባሉት አቃቤ ሕግም ለአንድ ቀን ታስረው መለቀቃቸው ተሰምቷል።

ግዳዩ የተፈጸመው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ደኖ ወረዳ ነው።ቀኑ ደግሞ ሚያዚያ 12/2010።

የወረዳው ኮማንድ ፖስትም ሶስት ተጠርጣሪዎችን ያስራል።ተጠርጣሪዎቹም ችሎት ይቀርባሉ።

ነገር ግን ተጠርጣሪዎቹ ስለተያዙበት ወንጀልም ፈጸሙት ስለተባለው ድርጊት የሚያስረዳ አካል አልተገኘም።

ስለዚህ ዳኛው አብነት ታደሰ የተጠርጣሪዎቹን ቃል ከሰሙ የሚያሳስራቸው ወንጀል ባለማግኘታቸው በነጻ ያሰናብቷቸዋል።

ተጠርጣሪዎቹን ያሰናበቱት ዳኛም ከወረዳው ከኮማንድ ፖስቱ ጽሕፈት ቤት በተላለፈው ትዕዛዝ መሰረት ዳኛው ከተጠሩ በኋላ በዚያው ወደ ወህኒ እንዲገቡ መደረጉም ታውቋል።

ዳኛው አብነት ታደሰ ለሚመሩት ችሎት ተጠርጣሪዎቹን ያቀረቡት አቃቤ ሕግም ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ለአንድ ቀን ታስረው እንዲፈቱ ይደረጋል።ምክንያቱ በግልጽ ባይታወቅም እንኳን።

ዳኛው አብነት እንደሚሉት ተጠርጣሪዎቹን በነጻ ሲያሰናብቱ ስለተጠረጠሩበት ወንጀል የሚያብራራም ሆነ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው አካል ማን እንደሆነ ባለመታወቁ ነው።

ስለዚህ ግለሰቦቹን ያሰራቸው ኮማንድ ፖስት ይሁን ወይንም ፖሊስ በውል ማረጋገጥ ባለመቻሉ የተጠርጣሪዎቹን ቃል ሰምተው በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰናቸውን ዳኛው ተናግረዋል።

ዳኛው አብነት ወደ ኮማድ ፖስቱ ጽሕፈት ቤት ተጠርተው ሲሔዱም በዳኝነት ሙያቸው ካስተላለፉት ውሳኔ ጋር የተያያዘ እንዳልመሰላቸውም ተናግረዋል።

የወረዳው ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትንም ቦታ በውክልና ስለምሰራ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ሲጠሩኝ የሔድኩትም ለአስተዳደራዊ ጉዳይ የፈለጉኝ መስሎኝ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ኮማንድ ፖስቱ በዳኝነት ባሳለፉት ውሳኔ ላይ ያላቸውን ያለመከሰስ መብት ወደ ጎን በማለት ወደ ወህኒ ለአራት ቀን እንዳወረዳቸው ተናግረዋል።

ከአራት ቀን እስር በኋላም ከእስር ቤት ወደ ጽሕፈት ቤቱ መወሰዳቸውንና በዛም አንድ የመከላከያ ሠራዊት ሻምበል፣ የወረዳው ፖሊስ አዛዥና የወረዳው የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ኃላፊ ሲጠብቋቸው እንዳገኙም ጠቅሰዋል።

በወቅቱም ለምን እንደታሰሩና ማን ትዕዛዙን እንዳስተላለፈው ሳይገለጽላቸው በደፈናው  ይቅርታ ብቻ ተጠይቀው መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ የወረዳው ፖሊስንም ሆነ ኮማንድ ፖስቱን ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አለመሳካቱ ታውቋል።