የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የያዘ አውሮፕላን የቴክኒክ ችግር ገጠመው

ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 917  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ይዞ ወደ ቤኒን ትላንት ሰኔ 8፣ 2004 ዓም የሁለት ሰዓታት ጉዞ ካደረገ በኃላ በአውሮፕላን የቴክኒክ ችግር ምክንያት ተመልሶ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ለማረፍ መገደዱን ምንጮቻችን ገለጹ፡፡

የእግር ኳስ ቡድኑ በነገው ዕለት ለ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከቤኒን ብሔራዊ ቡድን ጋር ላለበት ጨዋታ በረራ የጀመረው ትላንት ከጠዋቱ 4፡45 ላይ ነበር፡፡ አብራሪው የቴክኒክ ችግር እንደገጠመው ሲያውቅ ለተጨዋቾቹ ሳያሳውቅ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ መወሰኑን ምንጫችን ጠቁሞ በዚህ ምክንያት በቡድኑ አባላት ላይ  መደናገጥ ወይም የሥነልቦና ችግር አልተከሰተም ብሏል፡፡

የበረራ ቁጥር 917 አዲስ አበባ ከተመለሰ በኃላ ጥገና ተደርጎለት ይኽው አውሮፕላን ከቀኑ 11፡05 ከአዲስ አበባ በድጋሚ ተነስቶ ቤኒን ከምሸቱ 4፡45 ላይ መድረሱን ምንጫችን ጨምሮ ገልጿል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ በነገው ዕለት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10፡00 ላይ ከቤኒን ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታውን ያካሄዳል፡፡

የኢትዮጽያ አየር መንገድ ወደ ቤኒን በረራ ሲያደርግ ትላንት የመጀመሪያው  እንደነበርም ታውቋል፡፡ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት በ2014 ብራዚል ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሴንትራል ሪፐብሊክ አፍሪካ ጋር በአዲስአበባ ስታዲየም ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 0 መርታቱ ያታወሳል፡፡ቡድኑ ቀደም ሲል ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 1 በመለያየት ካገኘው ነጥብ ጋር ተደምሮ ምድብ አንድን በአራት ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide