በግፍ እስር ላይ የሚገኙት እነ አንዱአለም አራጌ የረሀብ አድማ እያደረጉ ነው

ሰኔ ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት በሽብር ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆነው ናትናኤል መኮንን፣ ክንፈ ሚካኤል በረደድ ( አቤ ቀስቶ) ፤ ምትኩ ዳምጤ እና ሌሎችም እስረኞች የረሀብ አድማ መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ካለፉት ሶስት ቀናት ጀምሮ እስረኞች ምንም አይነት ምግብ አልቀመሱም፤ ከቃሊቲ የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተውም አድማው ለአንድ ሳምንት ያክልም ይቀጥላል።  በጣም ቅርብ ከሆኑ ቤተሰቦቻቸው በስተቀር የትግል አጋሮቻቸውና አድናቂዎቻቸው እስረኞቹን  እንዳይጎበኙዋቸው ተከልክሏል። በአቶ አንዱአለም ላይ ከደረሰው ድብደባ በተጨማሪም በቅርቡ አቶ ኦልባና ሊሌሳ መደብደባቸው ታውቋል።  እስረኞቹ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ በደል እየደረሰባቸው ሲሆን አድማውም ቀይ መስቀል እንዲጎበኛቸው እና አያያዛቸው እንዲሻሻል ለመጠየቅ  ተብሎ የሚደረግ ነው። በዛሬው እለት በተወሰኑ እስረኞች ላይ መጠነኛ አካላዊ የመድከም  ስሜት እንደታየ፣ መንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ግን አሁንም አለመነካቱን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጠዋል። የእስር ቤቱ ሀላፊዎች እሳከሁን ድረስ ለጥያቄያቸው መልስ አልሰጡም። የእስረኞቹ የረሀብ አድማ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት እንዳያገኝ መረጃውን ለማፈን ሙከራ መድረጋቸውም ታውቋል።

ከጥቂት ሳምንታት በሁዋላ ውሳኔ የሚተላለፍባቸው እነ አንዱአለም   ከፍርድ ቤቱ ፍትሀዊ ፍርድ እንደማይጠብቁ በተደጋጋሚ ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወቃል።

በሌላ ዜና ደግሞ አሜሪካዊው ሴናተር ፓትሪክ ሊህ  በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለውን የፕሬስ አፈና አውግዘዋል፣ በእስር ላይ የሚገኙትን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ሴናተሩ በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በማውገዝ እና ጋዜጠኞች እንዲፈቱ በመጠየቅ   ሶስተኛው የኮንግረስ አባል ናቸው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide