የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተወያዩ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 27/2010) የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር መነጋገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አስፈላጊ ኮሚቴ አባላት በተጨማሪ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሃላፊዎችንም አነጋገረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለቱንም ወገኖች በተናጠልና በጋራ ማወያየታቸውን ተከትሎ ሁለቱም ወገኖች ችግሮቻቸውን የእስልምና አስተምህሮቶቻቸውን መሰረት አድርገው ለመፍታት መስማማታቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው፣በአሸባሪነት ተከሰው ወደ ወህኒ መጋዛቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን እስራት ለመመርመር በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ የተላኩ የአሜሪካ ልኡካን፣ታሳሪዎቹ የመብት ጥያቄ በማንሳታቸው መታሰራቸውን ይፋ ማድረጋቸውም አይዘነጋም።

የአሜሪካ የሃይማኖቶች ነጻነት በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ የመንግስት ባለስልጣናትንና የተለያዩ ወገኖችን ጭምር ካነጋገረ በኋላ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ይታወሳል።

በአሸባሪነት ተከሰው ለአመታት ወህኒ የቆዩት የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላቱ በኢትዮጵያ ከተፈጸመው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በተደረገው ግፊት መፈታታቸው ይታወሳል።