አዳዲስ ፕሬዝዳንቶች ተሾሙ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 27/2010) ለኢትዮያ ንግድ ባንክና ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዳዲስ ፕሬዝዳንቶች ተሾሙ።

አቶ ባጫ ጊና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ሲደርጉ አቶ ሃይለማርያም በቀለ ደግሞ የልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸው ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ካለፉት ሶስት ወራት ጀምሮ በሃገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሚካሄደው ብወዛ የሃገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ገዢን በማንሳት ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ለረጅም አመታት ያገለገሉት አቶ ተክለወልድ አጥናፉና ምክትላቸው ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል።

የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ይናገር ደሴ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው ሲሾሙ፣ለረጅም አመታት የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት አቶ በቃሉ ዘለቀ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሆነዋል።

የሃገሪቱ ግዙፍ ባንክ የሆነውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ አቶ ባጫ ጊና ትላንት ተሹመዋል።

አቶ ባጫ የኦሮሚያ ሕብረት ስራ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደነበሩም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለረጅም አመታት በፕሬዝዳንትነት የመሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ ቢሆኑም የባንኩን የቦርድ ሊቀመንበርነት ስፍራ አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ በረከት ስምኦን ስለተፈራረቁበት አድልዎና ሕገ ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸምበት መቆየቱን የባንኩ ምንጮች ሲገልጹ ቆይተዋል።

አሁን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የሆኑት አቶ በቃሉ ዘለቀም በፕሬዝዳንትነታቸው ከሌሎቹ ጋር ተባባሪ በመሆናቸው በህግ ሊጠየቁና የያዙትን ስልጣን ሊያጡ እንደሚችሉ እየተገለጸ ይገኛል።

የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/አባል በሆኑት በአቶ ኢሳያስ ባህረ ከፍተኛ ምዝበራ እንደተፈጸመበት የሚነገረው የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ዛሬ አዲስ ፕሬዝዳንት ተሹሞለታል።

ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ሃይለኢየሱስ በቀለ በዚሁ ባንክ ውስጥ የክሬዲት ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩ ናቸው።

ከጋምቤላ እርሻ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሃገር ሃብት የባከነበትና 5 ቢሊየን ብር ያህል በአጭር ግዜ ያጣው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ከአመት በፊት ከስልጣን ተነስተዋል።

በምትካቸው የተሾሙት የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ የነበሩት አቶ ጌታሁን ናና ባለፈው ግንቦት ወር በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን ለቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ በአቶ ኢሳያስ ባህረና በሌሎች የልማት ባንክ ሃላፊዎች ላይ ምርመራ ተጀምሯል።

ሆኖም አቶ ኢሳያስ ባህረ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ሳይወጡ ከሃገር ወጥተዋል።