ህዳር 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የዎርልድ ፕሬስ ጋዜጠኛ የመሬት ቅርምትና የአለም ባንክ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ በኢትዮጵያ የዉጭ ኢንቬስትሜንትን ለማዳበር ከነበረዉ ፍላጎት አንፃር የአገሪቱን ለም መሬቶች ለዉጭ ባለሃብቶች ለመስጠት የተወሰደዉ እርምጃ ማህበራዊ፤ አካባቢያዊና የህዝቡን የምግብ ፍላጎት ለመጠበቅ በሚያስችል ሁኔታ አለመፈፀሙን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሰት በመሬት ቅርምቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ገበሬዎች እንደሌሉ ቢገልፅም በጋምቤላና በቤንሻንጉል ክልል 45 ሺህና 90 ሺህ ሰዎች በቅደም ተከተል በመንደር ምስረታና በመሬት ቅርምቱ ምክንያት እንደተፈናቀሉ፤ እንዲሁም 650 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች የኑሮ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የተናጋ መሆኑን የኦክላንድ ኢንስቲትዩት በተጨባጭ የደረሰበትን ሃቅ መካድ እንደማይቻል ፀሃፊዉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለማሳመን እንደሚሞክረዉ ሳይሆን የአካባቢዉ ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት ምንም አይነት ማረጋገጫ እንደሌለ ጥናታዊ ፅሁፉ ይገልፃል።
በህዝቡ የአኗኗር ሁኔታ ላይ የደረሰዉን ዉድቀት፤ ከመሬቱ በመፈናቀሉ በማንነቱና በባህሉ ላይ ሊከተል የሚችለዉ ቀዉስ፤ የምግብ ዋስትና ማጣቱና፤ ከተፈጥሮ ሃብት ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለዉን ግጭት፤ ከወዲሁ መገመት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን አብራርተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ 7 ቢሊዮን የደረሰዉ የአለም ህዝብ ቁጥር በ2050 9.2 ቢሊዮን እንደሚደርስና አሁን ካለዉ 70 በመቶ ያህል ተጨማሪ ምግብ እንደሚያስፈልግ በመግለፁ፤ በሌላም በኩል የአየር ንብረት ለዉጥ ..ድርቅ… የጎርፍና የእሳት አደጋ እንዲሁም የኑሮ ዉድነት የምግብ እጥረትን ሊያስከትሉ በመቻላቸዉ የእርሻ መሬት ቅርምት በሰፊዉ በመካሄድ ላይ እንዳለ ጠቁመዋል።
እስያና መካከለኛዉ ምስራቅ የእርሻ መሬቶችን ተቀራምተዉ ምግብ ለህዝባቸዉ አምርተዉ ማቅረብና በሌላም በኩል መንግስታዊና የግል ኢንቬስተሮች የምግብ እህሎችንና የባዮ ነዳጅ ምርቶችን በትርፍ ለገበያ ለማቅረብ፤ ከታክስና ቀረጥ ነፃ የሆኑ እንዲሁም ርካሽ ጉልበት የሚገኝባቸዉን ሁዋላ ቀር አካባቢዎች መቀራመት ጠቃሚ ሆኖ ማግኘታቸዉን ፀሃፊዉ አብራርተዋል። የአለም ባንክ ሃላፊነት የሚሰማዉ የግብርና ኢንቬስትሜንት ደንቦች ቢያወጣም ተግባራዊ ሊያደርግ አለመቻሉ በጥናቱ ላይ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና የሌላት፤ እኤአ በ2009 7.8 ሚሊዮን የሚሆነዉ ከጠቅላላዉ ህዝቧ 10 በመቶ የሚሆነዉ አሳሳቢ በሆነ ረሃብ ዉስጥ የወደቀ መሆኑ ተገልጿል። የ2010 የአለም የምግብ ዋስትና ደረጃ ሰንጠረዥ ጥናቱ ከተደረገባቸዉ 162 አገሮች ኢትዮጵያ በ6ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ማሳየቱን ይኸዉ የዎርልድ ፕሬስ ርፖርት ጠቅሷል።