መንግስት የየኔሰው ገብሬን ሞት ለመሸፋፋን ከፍተኛ ሩጫ እያደረገ ነው፣ ማንም ሰው ከዬኔሰው ቤተሰቦች ጋር እንዳይገናኙ መከልከሉ ታወቀ

ህዳር 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዲሞክራሲና ፈትህ በሌለበት አገር አልኖርም በማለት በዋካ እራሱን በእሳት በማቃጠል የገደለውን የየኔሰው ገብሬን ሞት ለመሸፋፋን ከፍተኛ ሩጫ በማድረግ ላይ የሚገኘው መንግስት፣ የአካባቢው ወጣቶችን ጨምሮ ማንም ሰው ከዬኔሰው ቤተሰቦች ጋር እንዳይገናኙ መከልከሉ ታወቀ

የበርካታ ልጆች አስተዳዳሪ የሆነችው  ታደለች በቀለ፣ ከማንኛው ሰው ጋር እንዳትገናኝ ለማድረግ ሰፈሩዋ በሙሉ በፖሊስና በደህንነት ሀይሎች 24 ሰአት ሙሉ እየተጠበቀ መሆኑን የገለጡት የአይን እማኞች፣ የወንድሟ መሞት ስቃይ የፈጠረባትን ያክል የመንግስት ባለስልጣናት ወንድሟን በሀሰት ስሙን እንድትበክል ለማድረግ የሚያደርጉት ሩጫ የአካባቢውን ሰው ይበልጥ ማስቆጣቱም ታውቋል።

በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ በሂሳብ ሹምነት የምትሰራው ታደለች፣ ወንድሜ “የእውቀት አባቴ፣ አስተማሪየ፣ ካቢኔዎች ወንድሜን ገደሉት” እያለች ስታለቅስ እንደነበር በለቅሶው ላይ የተገኙ ነገር ግን ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ሰዎች  ተናግረዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት እህቱን ከማስገደድ አልፈው የተርጫ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች የሆኑትን ዶ/ር ወንድማገኝ እና ዶ/ር ሞይን “የኔሰው የሞተው በአእምሮ በሽታ ነው ብላችሁ ጻፉ” በማለት ለማስገደድ ቢሞክሩም ሁለት ዶክተሮች ግን አሻፈረን ማለታቸው ታውቋል። ዶ/ክተሮቹ እኛ ያላከምነውን ሰው አክመናል ብለን ብንናገር ሙያውና ህጉ አይፈቅድልንም ብለው እንደመለሱ ለማወቅ ተችሎአል።

የመንግስት ባለስልጣናት ጉዳዩን ለማስተባበል እየሄዱበት ያለው የተሳሳተ መንገድ የአካባቢውን ህዝብ ለማሳመን እንዳልቻለና ህዝቡ ለባለስልጣናቱ ውትወታ ጆሮ እንዳልሰጠው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አካባቢው ነዋሪ ገልጠዋል

ነዋሪው የመምህር የኔሰው ሞት ተራ ሞት ከሆነ ለምን የመንግስት ባለስልጣናቱ መሩዋሩዋጥ አስፈለጋቸው፣ ሲሉ ይጠይቃሉ።