ኢትዮጵያ ጦሩዋን መልሳ ወደ ሶማሊያ ለማስገባት ከፍተኛ ፍላጎት ማሳየቱዋን የአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ገለጡ

ህዳር 8 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኒውዮርክ ታይምሱ ጄፍሪ ጀንትልማን እንደዘገበው የኢትዮጵያ ጦር በአልሸባብ ሰራዊት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ይችል ዘንድ የኢትዮጵያን ሰራዊት መልሶ  ለማስገባት እያሰበ ነው።

አንድ የሶማሊያ  ባለስልጣን ግን የኢትዮጵያ ጦር የሸክ ሸሪፍ አህመድን መንግስት ለመደገፍ በሚል ሰበብ ወደ ድንበሩ ዘልቆ መግባቱን ተናግረዋል።

የምእራብና የአፍሪካ ህብረት  ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ውሳኔ በሶማሊያ ውስጥ የስልጣን ሽሚያ ስለሚፈጥርና ኢትዮጵያም የራሱዋን መንግስት የማቋቋም ፍላጎት ስለምታሳይ አገሪቱን ይበልጥ ያተራምሳታል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጠዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል የአልሸባብ ሰራዊትን ከሞቃዲሾ ማስወጣት ስላልቻለ የኢትዮጵያን ጦር ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሼክ ሸሪፍ አህመድ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲገባ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ጋዜጣው ዘግቦ፣ ይሁን እንጅ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ለመቃወም ምንም አይነት ጉልበት እንደሌላቸውና ውሳኔውን አምነው ከመቀበል ውጭ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ጋዜጣው ኢትዮጵያ ፣ ዩጋንዳና ኬንያ የምእራባዊያንን እርዳታ ለማግኘት ሲሉ በሶማሊያ እጃቸውን ማስገባታቸውንና የራሳቸውን ተጽእኖ ለመፍጠር እየተሩዋሩዋጡ ነው ብሎአል።

ኬንያ ሰሞኑን ከእስራኤል ጋር አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል ያደረገችው ስምምነት አልሸባብ በሀይማኖት ሰበብ በርካታ ሰራዊት እንደሚለምል እንደረዳው ጋዜጣው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ጦር ከአምስት አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በሁዋላ በሁለት አመት ቆይታው ይህ ነው የሚባል የጸጥታ ስራ ሳይሰራ መመለሱ ይታወቃል።

ሂውማን ራይትስ ወችን የመሳሰሉት ድርጅቶች የመለስ መንግስት በሶማሊያ ህዝብ ላይ ላደረሰው ጥፋት በጦር ወንጀለኝነት እንዲጠዬቅ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያን ጦር ወጪ ማን እንደሚሸፍነው ጋዜጣው አልጠቀሰም።