የመምህር የኔሰው ገብሬ አሟሟት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግፍ አገዛዝ የደረሰበትን ደረጃ ያሳያል ሲሉ ኢትዮጵያውያን ገለጡ

ህዳር 9 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፍትህ፣ ዲሞክራሲና ነጻነት በሌለበት አገር አልኖርም በማለት እራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው መምህር የኔሰው ገብሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግፍ አገዛዝ የደረሰበትን ደረጃ ያሳያል ሲሉ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ገለጡ

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊስት ( ኦፌዴን) ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ነገአ ለኢሳት እንደተናገሩት ፤ የየኔሰው ሞት አስደንጋጭ ዜና ቢሆንባቸውም፤ የእኛ አገር ጭቆና ምን ያክል ደረጃ እንደደረሰ፣ ሰዎች ህይወታቸውን ጭምር መስዋት ለማድረግ እንደማይመለሱ ያሳየ ነው ብለዋል

የመኢአድ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልና የሰሜን ጎንደር አደራጅ የሆኑት አቶ ያሬድ ግርማ በበኩላቸው መምህር የኔሰው ታላቅ የመንፈስ ልእልና ተጎናጽፎ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ትልቅ መስዋትነት የከፈለ ነው ብለዋል።

በሀረርጌ ነዋሪ የሆኑትና የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሀላፊ የሆኑት አቶ አምደ ስላሴ የኔሰው ለሁሉም ህዝብ አርአያ ሆኖ ማለፉን ገልጠው፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰው ልጅ ክብር የማይሰጥ በመሆኑ የሟቹን ታሪክ ለማንቋሸሽ መሞከሩን ተናግረዋል።

በወላይታ ከተማ የምትኖረው ጸሀይ ተሰማ ደግሞ የየኔሰው ሞት አሳዛኝ ቢሆንም፣ በእርሱ ሞት ሌሎች ቢያልፍላቸው ጥሩ ነው ስትል ተናግራለች።

በሰሜን ወሎ ነዋሪ የሆነው ነጻነት ግሩም በበኩሉ የወጣት የኔሰውን መሞት ድንጋጤ ና ቁጭት እንደፈጠረበት ተናግሯል።

በስዊድን ከተማ የሚኖሩት የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት አቶ ፍሰሀ ተሰማ በቅርብ የሚያውቁት የኔሰው ገብሬ ሞት እንዳስደነገጣቸው ገልጠው ልጁ የሰራውን አኩሪ ስራ ለመሸፋፈን የሚደረገው ጥረት ሩቅ እንደማያስኬድ ተናግረዋል።