ነሃሴ ፳፰(ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ ሰማያዊ ፓርቲ ሊያደርገው የነበረውን የተቃውሞ ሰልፍ በሀይል የጨፈለቀው የ ኢህአዴግ መንግስት፤ በርካታ የፓርቲውን አባላት እንዳሰረ ፣ እንደደበደበና እና የጽህፈት ቤቱን ንብረት እንደመዘበረ ፓርቲው መግለጹን ቢቢሲ በትናንት ዘገባው አመልክቷል።
የፓርቲውን ሊቀመንበር ይልቃል ጌትነትን በመጥቀስ የዜና አውታሩ እንደዘገበው፤ እሁድ ሊካሄድ ለነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በፓር ቲያቸው የተዘጋጁ የድምጽ መሣሪያዎች በታጣቂዎች ተወስደዋል፤ ሰልፉም እንዳይካሄድ በሀይል ተቀልብሷል።
ስለጉዳዩ በቢቢሲ የተጠየቁት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚ/ር ዲኤታ አቶ ሽመልስ ከማል ድርጊቱ አልተፈጸመም ሲሉ ክደዋል።
አቶ ሽመልስ አክለውም ሰማያዊ ፓርቲ በሰኔ ወር የጠራው ህዝባዊ ተቃውሞ በ1997 ከተደረገውና የመቶዎችን ህይወት ከቀጠፈው ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ነበር::
ፓርቲው በባለፈው የተቃውሞ ሰልፍ የመብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞች ከእስር እንዲፈቱ የጠየቀ ሲሆን፤ ለ እሁድ ሊያደርገው አስቦት የነበረው ሰልፍ ደግሞ የፓለቲካ ታሃድሶ እንዲካሄድ ጥሪ የሚያደርግ ነበር::
አቶ ሽመልስ -” ማንኛውም ህዝባዊ ተቃውሞ የሚያደርግ አካል ፍቃድ ማግኘት አለበት ፤ሆኖም ባለሥልጣናት ፈቃድ መከልከል አይችሉም፤ ነገርግን ተቃውሞው በሌላ ቦታና ጊዜ እንዲካሄድ መንግሥት የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል::
መለስ ከሞቱ በኋላ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሚመሩዋት ኢትዮጵያ ባለችበት ቀጣና እስላማዊ አማጺያንን በመዋጋት የአሜሪካ አጋዥ ነች ብሏል-ቢቢሲ።
አቶ ሽመልስ-መንግስት በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተባለውን ነገር አልፈጸመም ብለው ለቢቢሲ በመናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል።
ሰማያዊ ፓርቲ ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓም የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።