ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች በድጋሜ ታላቅ ግብዣ ተዘጋጀ

ነሃሴ ፳፰(ሃያ ስምንት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአራት ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የወጣበትና በኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት የኪነጥበባት ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የሚዲያ ባለሙያዎች ቡድን የተሳተፉበት የጉብኝት ፕሮግራም ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 4/2005 ዓ/ም በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን ይህንን መነቃቃትና የገጽታ ግንባታ አጠናክሮ ለመቀጠል ያስችላል የተባለ ታላቅ ድግስ ጳጉሜ 3 ቀን 2005 በሸራተን ሆቴል ተዘጋጀ፡፡

አርቲስቶችና ጋዜጠኞች የተሰባሰቡበት ይህው ቡድን በወቅቱ በሶማሌ ክልል ከጎዴ ጀምሮ እስከ ጅጅጋ ድረስ ጉብኝት ያካሄዱ ሲሆን ይህንን ተከትሎም አብዛኛው የቡድኑ አባላት ቀጣይ የስነጥበብ ዝግጅት በአዲስአበባ ለማድረግ በመስማማት በቅርቡ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በአቶ ካሳ ተክለብርሃን የሚመራው የፌዴሬሽን ም/ቤት በዚሁ የተገኘውን ሰፊ መነቃቃትና የገጽታ ግንባታ ይበልጥ ለማዳበር በሚል ሰሞኑን ታላቅ የእራት ግብዣ ጠርተዋል፡፡ በዚህ ግብዣ ላይ የተለያዩ የፌዴራልና የክልል የመንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ የስነጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ይገኛሉ ተብሎአል፡፡

በሶማሌ ክልል የተሳካ ጉብኝት መካሄዱን እነአቶ ካሳ ተ/ብርሃን አረጋግጠናል ካሉ በኃላ ቡድኑን ይመሩ ከነበሩት አርቲስቶች መካከል የአቶ ካሳ ተ/ብርሃን የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ሽመልስ ለውለታቸው ብሔራዊ ቲያትርን በስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡

በእነአርቲስት ሰርጸፍሬ ስብሃት የሚመራና የአርቲስቶች ቡድንም በቅርቡ በሶማሌ ክልል ላይ ያተኮረ የስነጥበብ ዝግጅት ለማካሄድ ተፍ ተፍ እያለ ነው፡፡