የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን አዲስ የዋጋ ታሪፍ ጭማሪ ማስተካከያ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን አዲስ የዋጋ ታሪፍ ጭማሪ ማስተካከያ ለማድረግ መወሰኑን አስታወቀ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ተጨማሪ የዋጋ ታሪፍ ሊጥል ነው። ከፍተኛ የኤሌትሪክ ፍጆታ ተጠቃሚዎች በአዲሱ ተመን እስከ 350 በመቶ ጭማሪ ክፍያ ይጠየቃሉ።
ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት (EEU)፣ ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ፓወር (EEP)፤ ከውሃ፣ መስኖ እና ኤሌትሪክ ባለስልጣን መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ጥናቱን ማድረጉን አስታውቋል።
በአዲሱ የዋጋ ማስተካከያ መሰረትም በፊት ድርጅቱ ከሚያገኘው ከ7 እስከ 10 ቢሊዮን ብር ገቢ ወደ 35 ቢሊዮን ብር ያስገባል ተብሎ ታቅዷል። የዋጋ ማስተካከያው ከ13 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መደረጉን የኢትዮጵያ መብራት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ ለካፒታል ጋዜጣ ተናግረዋል።
ዋና ስራስኪያጇ አዲሱ የዋጋ ጭማሪ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙትን የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ ከለላ ይሰጣል ብለዋል። ‘’በአጠቃላይ 2.9 ሚሊዮን ደንበኞች አሉን። ከእነዚህ ውስጥ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑት ከ50 ኪሎ ዋት በታች ተጠቃሚዎች ናቸው። በእኛ ጥናት መሰረትም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ ቁጥርም ከአጠቃላይ ደንበኞቻችን ሃምሳ በመቶውን ቁጥር ይይዛል’’ ብለዋል፤
ለከፍተኛ የኤሌትሪክ ፍጆታ ተጠቃሚዎች ለሆኑት በፊት በአንድ ኪሎ ዋት በዶላር 7 ሳንቲም የነበረው ወደ 1.8 የሜሪካ ዶላር ከፍ ይላል። የዋጋ ጭማሪው ከብር የመግዛት አቅም መውረድ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና የዋጋ ማስተካከያው በፍጥነት በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እንደማይሆንም አስታውቀዋል። በተጨማሪም ወደ ክፍያ ከመገባቱ አስቀድሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አዎንታዊ የሆነ ውይይት እንደሚካሄድና የዋጋ ተመኑ በዓለም ላይ ዝቅተኛ ክፍያ መሆኑን መናገራቸውን ካፒታል ጋዜጣ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ ጊዜያት የመብራት መቆራረጥ ችግሮችን በመፍጠር ደንበኞቹን እያማረረ ነው። ይህንን መሰረታዊ ችግሩን ከመቅረፍ ይልቅ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ መሽቀዳደሙ እንዳስገረማቸው ታዛቢዎች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው። እየተዳከመ በመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ የተደረገው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተግባራዊ ከሆነ ጫና ሊፈጥር ይችላል ተብሎም ተሰግትዋል።