በጅግጅጋ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ባንዲራና መገንጠልን የሚቀሰቅሱ ባነሮች በብዛት እየታተሙ መሆናቸው ተገለጸ። ኮማንድ ፖስቱ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

በጅግጅጋ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ባንዲራና መገንጠልን የሚቀሰቅሱ ባነሮች በብዛት እየታተሙ መሆናቸው ተገለጸ። ኮማንድ ፖስቱ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ/ም ) በስፍራው ያሉ የኢሳት ወኪሎች ባደረሱን መረጃ መሰረት፣ ቀደም ሲል አብዲ ኢሌ ያደራጃቸው ሄጎ የእተባሉ የሚጠሩት ቡድኖች፤ ትናንትና በጅግጅጋ ከተማ የመንግስት መኪኖችን ጭምር በመጠቀም እና የኦብነግን ባንዲራ በማውለብለብ ብጥብጥ ለመፍጠር ሞክረዋል።

እነዚሁ ቡድኖች ክልሉን ለማረጋጋት ከተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭት መፍጠራቸውን ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት በመሳሪያ ኃይል የበተኗቸው ሲሆን፣ በተኩስ ልውውጡ በፖሊስ መኪና ላይ የኦብነግ ባንዲራ ሰቅሎ ሲያሽከረክር የነበረ የሂጎ አባል ቆስሏል። የሶማሌ ልዩ ፖሊስ ሰሞኑን በሀረርጌ በከፈቱት ድንገተኛ ጥቃት 41 ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል።
ምንጮች እንደሚሉት ከሂጎዎ ጋር የተፋጠጠው መከላከያ ብቻ አይደለም። ህዝቡም የቡድኑ አባላት እየፈጸሙት ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመመከት ባለ በሌለ አቅሙ እየታገላቸው ነው። በትናንትናው ዕለት ሕዝቡ ከሂጎዎች ጥቃት ድንጋይ በመወርወር ራሱን ሲከላከል መከላከያ ሰራዊት ወደቦታው ደርሶ ግጭቱን ቢያበርድም፣ ሂጎዎቹ በፍጥነት በመኪና ከአካባቢው ተሰውረዋል።
አዲስ የተቋቋመው የክልሉ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ጄነራል ሀሰን፣ የኦጋዴ ብሄራዊ ነጻነት ግንባር ኦብነግ ራሱን ሂጎ ከሚባሉት በመለዬት እና የቡድኑን አባል ስርዓት አልበኝነት በማውገዝ የለውጡን ሂደት እንዲያግዝ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ አምስት በሚደርሱ እና በአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች የሚመሩ ማተሚያ ቤቶች “ኦብነግን ለመቀበል” በሚል የሶማሊያ ሪፐብሊክ ባንዲራ እየታተመ ነው። ይሕ እየተደረገ ያለው፤ የልዩ ፖሊስ አዛዥ አብዱራህማን ወንድም እና የሂጎ መሪ በሆነው በአብዱላሂ ትዕዛዝ ነው ይላሉ ምንጮቹ። ከባንዲራውም በተጨማሪ መገንጠልን የሚቀሰቅሱ እጅግ በርካታ ባነሮች እየታተሙ መሆናቸው ተመልክቷል።
ጉዳዩ ያስቆጣቸው የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች ኦብነግ ይህን ስርዓት አልበኝነት ያውግዝ ሲሉ አሣስበዋል። የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች አክለውም “እንዲህ ያለውን ሁኔታ አንታገሰውም” በማለት አስጠንቅቀዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊዎች ከህዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይትም ፣ በአብዲ ኢሌ ደጋፊዎች እየተሰራጨ ያለውን ይህን ፕሮፖጋንዳ በጋራ በማውገዝ የተገኘውን ሰላም እና የለውጥ ተስፋ እንዳይቀለበስ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ቆመው እንደሚታገሉ አረጋግጠዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች እና የክልሉ ምሁራንም በግጭቱ የተጎዱትን መልሶ ለማቋቋም እየሰሩ ሲሆን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያኖችም ተመልሰው እንዲሰሩ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።