አቶ ተስፋዬ ኡርጌ እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ምርመራ ተጀመረባቸው

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 9/2010) የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባለስልጣን የነበሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ካሉ ግጭቶች ጋር በተያያዘም ምርመራ እንደተጀመረባቸው ተገለጸ።

አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የሰኔ 16ቱን የቦምብ ጥቃት በማስተባበር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል።

ግለሰቡ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የግዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ወደ ወህኒ ቤት ተመልሰዋል።

ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በውጭ ሃገር ካሉ ቡድኖች ጋር አላቸው በሚል የተጀመረባቸው ምርመራም መቀጠሉ ተመልክቷል።

ሰኔ 16 ቀን 2010 በአዲስ አበባ ከተማ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ ለማድረግ በተጠራውና ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ሕዝባዊ ትዕይንት በተወረወረ የእጅ ቦምብ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።ከ150 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።

ከዚህ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ በዕለቱ በቂ ጥበቃ አላደረጉም ክፍተት ትተዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነርን ጨምሮ 10 ያህል ከፍተኛ የፖሊስ ሃላፊዎችም ታስረው ነበር።

እነዚህ የፖሊስ ሃላፊዎች ትላንት እስከ 15 ሺህ ብር ዋስ ጠርተው እንዲወጡ ፍርድ ቤቱ ሲወስን በመወርወርና በማስተባበር የተጠረጠሩት ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

የሒደቱ ዋና አስተባባሪ እንዲሁም በውጭ ከሚገኙ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ሒደቱን በበላይነት መርተዋል የተባሉት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሃላፊው ላይ የተጀመረው ምርመራ ግን ቀጥሏል።

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት ውስጥ በሃላፊነት ሲያገለግሉ የቆዩትና ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከተጠረጠሩበት የሰኔ 16ቱ ፍንዳታ ባሻገር በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ግጭቶች ውስጥ በመጠርጠራቸውም በዚህም ዙሪያ ምርመራ መጀመሩን ፖሊስ ዛሬ ለፍርድ ቤት አስታውቋል።

ግለሰቡ በውጭ ካሉ ቡድኖች ጋር የፈጠሩት ግንኙነት እንዲሁም ከገቢያቸው በላይ ሃብት አካብተው ከመገኘታቸውም ጋር ተያይዞ ሰፊ ምርመራ እንደተጀመረባቸው ተመልክቷል።

ፍርድ ቤቱም ለተጨማሪ 14 ቀናት ምርመራ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቶ ግለሰቡን ወደ ወህኒ ቤት እንዲመለሱ አድርጓል።