የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ ሰራዊት በጋራ ወታደራዊ ጥቃት ፈፀሙ

ህዳር ፲፮(አስ ስድስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :- የጋራ ትግል አስፈላጊ መሆኑን በፅኑ የሚያምኑት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር  እና የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ  በሕዳር 13/2006 ዓ.ም በሁመራ ሉግዲ ከቀኑ    10፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1፡00 ለሶስት ሰዓት ያህል በወሰደው ውጊያ የመንግስት 24ኛ ክፍለ ጦር ድባቅ ተመቷል ብሎአል።

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በ24ኛው ክፈለ ጦር ላይ በተመሳሳይ ሥፍራ  ከፍተኛ ድል መቀዳጀቱ ይታወሳል።

በሕዳር 13/2006 ዓ.ም የኢሕአግና የጋህነን ሰራዊት በወሰዱት ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃት 66 ወታደሮችን ገድለው 113 በማቁሰል እንዲሁም ቁጥራቸው የበዛ የጦር መሳሪያዎችን ከነ ሙሉ ትጥቃቸው ማርከዋል።

በውጊያው ከሞት ተርፎ ለከባድ ቁስልና የአካል ጉዳት የተዳረገው የ24ኛ ክፈለ ጦር አባላትን ከሁመራ አንስቶ እስከ ትግራይ የሕክምና ማዕከሎች ማጋጋዝ ዋነኛ ተግባሩ ሆኗል ብሎአል ግንባሩ ለኢሳት በላከው መግለጫ።

አርበኞች ግንባር እና የጋምቤላ ህዝብ ንቅናቄ አገኘው ባሉት ድል ዙሪያ የመንግስትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ።