የአፍሪካ የካረቢያንና የፓስፊክ አገራት ፓርላማ ጉባዔ

ህዳር ፲፮(አስ ስድስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-የአፍሪካ ኅብረት በዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ላይ የያዘውን አቋም እንዲደግፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ጥያቄ አቀረቡ፡፡

ጥያቂያቸውን ለመቀበል አውንታዊ ምላሽ እንደገኙ በመግለጽ አፈጉባኤው ለጋዜጠኞች ቢናገሩም ጉዳዩ ተቀባነት ያገኘው ለውይይት እንጅ ለማጽደቅ አይደለም ተብሎአል።

የአፍሪካ የካረቢያንና የፓስፊክ አገራት ፓርላማ 34ኛ መደበኛ ጉባዔ ትላንት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በተካሄደበት ወቅት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ” ዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአፍሪካ መሪዎችን ለዓለም ዓቀፉ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እየተንቀሳቀሰ ነውና ይህንን ሃሳብ እንድናቀርብ ይፈቀድልን” በማለት አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይህንኑ እንቅስቃሴ ስትቃወም መቆየቷንና በቅርቡም የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ተመሳሳይ አቋም መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ኅብረት ዓለም ዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በአፍሪካ በሕዝብ የተመረጡ መሪዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚያካሂደው እንቅስቃሴ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው የሚል አቋም እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡

ይህንን የአፍሪካ ኅብረት አቋም በመያዝ ከአፍሪካ የተውጣጡ ተወካዮች ወደ አሜሪካ ኒውዮርክ በመጓዝ ለጸጥታው ምክር ቤት ማቅረባቸውንም አክለዋል፡፡

የአፍሪካ፣ ካረቢያንና ፓስፊክ ፓርላሜንታዊ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጆይስ ላቦሶ የአፍሪካ የካረቢያንና የፓስፊክ አገራት ፓርላማ 34ኛ መደበኛ ጉባዔ በአባል አገራቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ፋይናንስና ንግድ ጉዳዮች እንዲሁም የማኅበራዊና አካባቢ ጉዳዮች በሚያቀርቧቸው ሪፖርቶችና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ ገልጸዋል፡፡

ጉባዔው ኮሚቴዎቹ በሚያቀርቧቸው ሪፖርቶችና በሌሎችም ዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይ በወያየት የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍም አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ፣ የካረቢያንና የፓስፊክ አገራት ቡድን ዋና ጸሐፊ አልሃጂ ሙሐመድ ሙሙኒ የአባል አገራቱ የፓርላማ አባላት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የሚያካሂዱት የጋራ ጉባዔ በዓለም ላይ በሰሜንና ደቡብ ፓርላማዎች መካከል የሚካሄድ ብቸኛው የፖለቲካ ውይይት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአፍሪካ፣ ካረቢያንና ፓስፊክ እና የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የጋራ ጉባዔ ላይ 200 ያህል የፓርላማ አባላት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ፣ ካረቢያንና ፓስፊክ ፓርላማ ሴክሬታርያት ገልጿል፡፡