በሳውድ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በመቃወም የሚደረጉ ሰልፎች ቀጥለዋል

ህዳር ፲፮(አስ ስድስት )ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአፍሪካ ፓርላማ  ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በተቃውሞው ላይ የተገኘችው የኢሳት የደቡብ አፍሪካ ተባባሪ ዘጋቢ ዝናሽ ሀብታሙ እንደገለጸችው በሰልፉ ላይ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ኢትዮጵያውያን ታሰትፈዋል።

ተቃውሞውን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ምክትል ሊ/መንበር አቶ ንብረት ጌታሁንም ህዝቡ በተቃውሞው ላይ ተገኝቶ ስሜቱን በከፍተኛ ሁኔታ ገልጿል ብለዋል በተመሳሳይ ዜናም የአፋር ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት፣ የሉቅማን ሙስሊም ማህበር እና የኢትዮጵያ ታስክ ፎርስ በአውሮፓ በቤልጂየም  ብራሰልስ በሳውድ አረቢያ ኢምባሲ ፊት ለፊት  ተቃውሞ አሰምተዋል። በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በዚህ ተቃውሞ በሳውዲ አረቢያ ለደረሰው ሰቆቃ መንግስት ተጠያቂ ነው፣ መንግስት በሳውድ አረቢያ ስደተኞች ስም መነገዱን ያቁም፣ መንግስትን እንፋረዳለን፣ በህዝብ ያልተመረጠ መንግስት ለዜጎች አይቆምም፣ የሳውዲ መንግስት አፈርንብህ የሚሉና  ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።

የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያስተባበሩ የነበሩት ለኢሳት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በጃፓንም ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።