የኢትዩጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ፊደራሊዝምን ባላከበረ መልኩ ያለ አግባብ ከክልሎች እንደሚሰበስብ ታወቀ

ጳግሜ ፭(አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ኤጀንሲ በቴሌቪዥን ቻናል አንድ እና ሁለት የአየር ሰዓት ድልድል ወጥቶላቸው በቀን የአንድ ስዓት ስርጭት የክልሎችን ተደማጭነት እና የልማት ዘገባ ለህዝቡ ለማድረስ ፣ እያንዳንዱ ክልል ለኢቲቪ በአመት አምስት ሚሊየን ብር በነፍስ ወከፍ ይከፍላል፡፡  የኢትዩጵያ ሬዲዩና ቴሌቪዥን በእየአመቱ ከክልሎች ብቻ 55 ሚሊየን ብር ገቢ ያገኛል፡፡

ክልሎች በራሳቸው ሳተለይት ተከራይተው ዝግጀቶቻቸውን ለማቅረብ ጥያቄ ቢያቀርቡም የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

በአሁኑ ስዓት በሳተላይት በራሳቸው ቻናል አየር ላይ የሚገኙት የሶማሌ እና የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ስርጭቶች በፍጥነት እንዲወርዱ በመንግስት ኮሚኒኬሺን ጉዳዮች ሚኒስትር በኩል  ማሰጠንቀቂያ ተላልፎባቸዋል፡፡

200 ሚሊየን ብር ወጭ ተደርጎበት በዘመናዊ ቴክኖሌጂ የተገነባው የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን በራሱ ቻናል ለመውጣት ያደረገው ሙከራም በመንግስት  እንዲታገድ ተድርጓል።

የቤኔሻንጉል ጉምዝ ክልል የቴሌቪዥን ፕሮዳክሺኑን የህወሀት ንብረት በሆነው በዋልታ ኢንፎርሜሺን ማዕከል ለማሰራት ለኢቲቪ ከሚከፍለው አምስት ሚሊየን ብር በተጨማሪ 25 ሚሊየን ብር ለዋልታ ይከፍላል፡፡

ሌሎች አዳጊ የተባሉ ክልሎችም እንዲሁ ዝግጅቶችንና ዘገባዎችን ለማሰራት ለዋልታ በእየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይከፍላሉ።

ኢቲቪ ከክልሎች የሚያገኘውን ገንዘብ ሳይጨምር በያዝነው አመት ከማስታወቂያ እና የአየር ስዓት ሺያጭ ብቻ ከ 43 ሚሊየን 420 ሺ ብር በላይ ገቢ አግኝቱዋል፡፡