በኢትዩጵያ 66 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች መፀዳጃ ቤት አልባ ናቸው

ጳግሜ ፭(አምስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የኢትዮጵያ ዌልፌር ሞኒተሪንግ ሰርቬይ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ 66 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች መፀዳጃ ቤት የላቸውም፡፡ መጸዳጃዎች ካሏቸው ውስጥ 2.2 በመቶ በውኃ የሚለቀቅ፣ 63.8 በመቶ ያህሉ በጉድጓድ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ በሜዳ ወይም በጫካ የሚጠቀሙት 33.7 በመቶ ያህሉን ይሸፍናሉ፡፡ በጫካ ወይም በሜዳ ከሚጠቀሙት 12.5 በመቶ ያህሉ በከተማ ሲሆን 39.5 በመቶው በገጠር አካባቢ ነው፡፡

ወተር ኤይድ ባወጣው መግለጫ መሠረትም በኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ በየሜዳው የሚፀዳዳ ሲሆን ሴቶች ደግሞ መፀዳጃ ፍለጋ በዓመት 3.4 ቢሊዮን ሰዓቶችን ያጠፋሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከ10 ሴቶች አራቱ የጥሩ መፀዳጃ ቤት ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ በመሆኑም ለእፍረት፣ ለፍርሃትና ለጥቃት ተጋልጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ መፀዳጃ ቤት በሌለበት አካባቢ የሚኖሩ ሴቶችና እናቶች መፀዳጃ ቦታ በመፈለግ በየዓመቱ 3.4 ቢሊዮን ሰዓት ያጠፋሉ ሲል ወተር ኤይድ ያስገነዝባል፡፡
በወተር ኤይድ ፖሊሲ ሴክተር ሀላፊ የሆኑ አንድ ግለሰብ፣ ” በገጠር በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎችና ባህሎች የሴት ልጅ በቀን ሜዳ ላይ መፀዳዳት እንደነውር በመቆጠሩ፣ ትምህርት ቤቶችም ሲገነቡ የመፀዳጃ ቤት አብሮ ባለመገንባቱ ወጣት ሴቶች በትምህርት ገበታ ላይ እያሉ ሳይሸማቀቁ ለመፀዳዳት የሚችሉበት ሁኔታ ባለመኖሩና ከወንድ ተማሪዎችም ትንኮሳ የሚደርስባቸው በመሆኑ ትምህርቱን እስከመጥላትና መቅረት የሚደርሱበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡

ባለስልጣኑ ፣ “ዓለም ዛሬ ከደረሰችበት ሥልጣኔ አኳያ ይህንን ችግር እንዲቀጥል ማድረግ የሚታሰብ አይደለም፤ የችግሩንም አስከፊነት በመገንዘብ ከፍተኛ የዓለማችን ፖለቲከኞችና የልማት አጋሮች በጋራ በመሆን ችግሩን ለማስገወድ በጋራና በተናጠል ለመሥራት የሚችሉበትን መንገድ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ” ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በየገበያ ቦታ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በምግብ ቤቶች እንዲሁም በጤና ጣቢያዎች ፅዱና አመቺ መፀዳጃ ቤት አለመኖር ኅብረተሰቡን እየጐዳው ጤናውንም እያወከው ነው፡፡ በተለይ በትምህርት ቤት የሚውሉ ሴት ተማሪዎች አመቺ የመፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ የወር አበባ በሚያዩበት ጊዜ ከትምህርት ለመቅረት እየተገደዱ ነው፡፡የሳኒቴሽን አገልግሎት ማግኘት ሰብአዊ መብት፣ ክብርና ደኅንነት በመሆኑ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳያው በኢትዮጵያ ከ60 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው በሽታ መነሻ መፀዳጃ ቤት በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው፡፡