አንድነት ፓርቲ በአዳማ/ናዝሬት የተሰካ የተቃውሞ ሰልፍ አደረገ

ጳግሜ ፬(አራት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ገዢው ፓርቲ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ከማውገዝ በተጨማሪ ህዝቡ ለእውነተኛ ለውጥ እንዲነሳ ጥሪ አድርጓል።

ሰልፈኛው ሲያሰማቸው ከነበሩት መፈክሮች መካከል ጥያቄያችን ህገመንግስታዊ ነው፣ ውሸት ሰልችቶናል፣ ስራ መግኘት መብታችን ነው፣ ጸረ ሽብር ህጉ በራሱ አሸባሪ ነው፣ መንግስት፣ የኑሮ ድጎማ ያድርግልን፣  ድህነት በወሬ አይጠፋም፣ ርእዮት አለሙ አሸባሪ አይደለችም፣ የታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞች ይፈቱ የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተሰምተዋል።

በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የከተማው ነዋሪዎች እና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተሳተፉበት በዚህ ሰልፍ ላይ በቅርቡ ራሳቸውን ከአንድነት የህዝብ ግንኙነት አመራር ቦታ ያገለሉት ዶ/ር ሀይሉ አርአያን ጨምሮ ሌሎችም ንግግሮችን አድርገዋል።

የአንድነትን ሰልፍ ለማደናቀፍ የከተማዋ ባለስልጣናት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተለያዩ ሙከራዎችን ቢያደርጉም፣ ፓርቲው ዝግጀቱን በጥሩ ሁኔታ አጠናቋል።

አንድነት ፓርቲ የጀመረው የሶስት ወር ዘመቻ መስከረም 5 በአዲስ አበባ በሚያደርገው የተቃውሞ ሰልፍ ይጠናቀቃል።