የኢህአዴግ መንግስት በኢምባሲ ውስጥ ገብተው የተቃወሙ ኢትዮጵያውያን እንዲከሰሱለት ጠየቀ

መስከረም ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ የአሜሪካ መንግስት የአገሪቱን ሰንደቃላማ በአወረዱ  ተቃዋሚዎች ላይ ክስ ይመሰርታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ተቃዋሚዎቹ ከኤርትራ መንግስት እና ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት አላቸው ብለዋል። የአሜሪካ መንግስት የኢምባሲውን ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነቱን አለመወጣቱን የገለጡት ቃል አቀባዩ፣ ተቃዋሚዎቹን ለፍርድ ያቀርባል ብለው እየጠበቁ መሆኑንም አክለዋል።

አምባሳደር ግርማ ብሩ ተቃዋሚዎቹ ክስ እንደሚመሰርትባቸው ገለጸው የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም የታየ ክስ የለም። በኢትዮጵያውያን ላይ ሽጉጥ የተኮሰው ኢምባሲ ሰራተኛ በ48 ሰአታት ውስጥ አሜሪካን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ ይታወቃል።  ድርጊቱ ለመንግስት ትልቅ የዲፕሎማሲ ሽንፈት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች መናገራቸው ይታወሳል።