የአንበሳ ከተማ አውቶቡስ ድርጅት ሰራተኞች የ8 ቀን ስልጠና ቅጣት ተጣለባቸው ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘገበ

መስከረም ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ስልጠናን ለ11 ቀናት የወሰዱት የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ሰራተኞች ስልጠናውን በደንብ አልተከታተላችሁም በሚል ተጨማሪ 8 ቀን እንዲሰለጥኑ ቅጣት ተጥሎባቸዋል ሲል የዘገበው ነገረ ኢትዮጵያ፣ ከመስከረም 19/2007 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30/2007 ዓ.ም በተሰጠው ስልጠና 4 ሺ 100 የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ሰራተኞች እንዲሰለጥኑ የተደረገ ሲሆን ሰራተኞቹ ግማሹን ቀን ሰልጥነው ግማሹን ቀን እንዲሰሩ መደረጉን አስታውሷል፡፡ ሰራተኞቹ ‹‹ስልጠናው የዕረፍት ጊዜያችን የሚሻማ ነው›› በሚል ስልጠናውን የተቃወሙ ሲሆን ስልጠናውን አቋርጠው በመውጣትና በመቅረት ተቃውሟቸውን መግለጻቸውንም ዘግቧል።

‹‹እያቋረጣችሁና እየቀራችሁ ስልጠናውን በሚገባ ባለመከታተላችሁ ተጨማሪ 8 ቀን እንድትሰለጥኑ ቅጣት ተጥሎባችኋል፡፡›› መባላቸውን ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል፡፡ ሰራተኞቹ ከነገ ጀምሮ እስከ ጥቅምት 8/2007 ዓ.ም በቅጣት የተጣለባቸውን ተጨማሪ ስልጠና ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

መንግስት ለጀመረው የፖለቲካ ስልጠና በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ብር ማውጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።