ግንቦት ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ባለስልጣናት ከፍተኛ ቀረቤታ በማሳየት በአፋር ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ትችት የሚቀርብባቸው አቶ ኢስማኤል አሊሰሮ በጀርመን ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
በህወሀት የደህንነት ሰዎች ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግላቸው አቶ እስማኤል ጤናቸው እየተሻሻለ መምጣቱን ለኢሳት ተናግረዋል። ” ተሽሎኛል፣ ጥሩ ህክምናም እያገኘሁ ነው፣ አላህ ከፈቀደ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ልመለስ እችላለሁ በማለት” ፕሬዚዳንቱ አክለዋል።
ፕሬዚዳንቱን በተለያዩ ጉዳዮች ለማነጋገር ብንሞክርም ጠባቂዎቻቸው ሊያገናኙን ፈቃደኞች አሎሆኑም።
በሌላ ዜና ደግሞ በገዋኔ አፋሮችና ከፌደራል ፖሊሶች ጋር ሲታኮሱ አንግተዋል።
የኢሳት አካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ከገዋኔ ከተማ አንድ ኪሎ ሜትር ወጣ ብላ በመትገኘዋ አዳሌ ገዋኔ ትናንት ከሌሊቱ 11 ሰአት እስከ ጧት አንድ ሰአት ድረስ የተኩስ ልውውጥ ተካሄዷል።
ግጭቱ የተከሰተው የፌደራል ፖሊሶች በሌሊት በድንገት ወደ አካባቢው በመሄድ በነዋሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈታቸው ነው። ፖሊሶቹ አቶ ሙሀመድ ሱላ በተባሉ ሽማግሌ ቤት ውስጥ በመግባት፣ ሽማግሌውን ደብድበው 2 መሳሪያዎቻቸውን ወስደውባቸዋል። በዚህ የተበሳጩት ነዋሪዎች በፌደራል ፖሊሶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውንና የተኩሱ ልውውጥ እስከ ንጋት መቀጠሉን የዜና ምንጮች ገልጸዋል። ከኢሳትዎች ጋር ግጭት የተፈጠረ የመሰላቸው አፋሮች ከየአካባቢው መሰባሰብ በመጀመራቸው ፖሊሶቹ አካባቢውን ለቀው ሄደዋል ።
ስቱዲዮ ከመግባታችን ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብሎ አንድ አግኝተን ስሜን አትጥቀሱ በማለት ፖሊሶቹ የፈጠሩትን ችግር በዝርዝር አስረድቷል
የፌደራል ፖሊሶች በአፋር ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያካሄዱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።