የአፋር ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት 9 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ገለጠ

ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንደጠቀሰው  የበሀይሌ ሊ/መንበር የሆኑት አቶ አሊ ማያቤ፣ የአካባቢው የጎሳ ተጠሪ የሆኑት አቶ ዳቶና ሙሀመድ ፣ አቶ አሊ ናስሪ ሙሀመድ፣ አቶ ኦማር ሀቴ፣ አቶ ዳውድ አሊ፣ አቶ ማያቢሄ ሞሀመድ፣ አቶ ካድር አስከሪ እና አቶ ሙሀመድ ኢጋሀሌ በፌደራል ፖሊስ ከተወሰዱ በሁዋላ እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም።

ድርጅቱ እንዳለው ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ በከፍተኛ ደረጃ ጨመሯል። በአሁኑ ጊዜ የአዳቢቶሊ፣ የገዋኒ፣ አሳይታ እና የበሀይሌ አካባቢዎች በመከላከያ ሰራዊት ተከበዋል። እንደ ድርጅቱ መግለጫ በቅርቡ የተነሳው ግጭት መንስኤ አንድ የመካላከያ ሰራዊት መኮንን እና  የሴት ጉዷኛው መገደላቸው ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች መኮንኑም ሆኑ ጓደኛው የተገደሉት በመከላከያ ውስጥ እርስ በርስ በተፈጠረ ሽኩቻ ነው ይላሉ። የመከለካያ አባላት ግን መኮንኑም ሆነ ሴት ጓደኛው የተገደሉት በአፋሮች ነው ብለው ያምናሉ። በዚህም የተነሳ የጋሊፋጌ መንደር ነዋሪዎች በወታደሮች እንዲከበቡ ከተደረገ በሁዋላ ታስረው አሰቃቂ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል። ከተሳሩት 13 ሰዎች መካከል ሁለቱ ተወስደው ተረሽነዋል። ከእነዚህም መካከል ሞሀመድ ሀቴ የተባለው ሟች አስከሬን ተቆራርጦ መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል። ካቢር ሀሰን የተባለው ሟች አስከሬን ግን እስካሁን አለተገኘም። ሁለቱም ግለሰቦች የተገደሉት ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ነው።

ድርጅቱ  በአፋር ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ሽብር በጥብቅ አውግዞ፣ ሟቾቹ በክብር እንዲቀበሩ፣ ገዳዮቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የክልሉ መንግስትም የሟቾችን ቤተሰቦች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል

ከሁለት ቀናት በፊት ኢሳት ስለደርጊቱ የዱብቲ ወረዳ ፖሊስ አዛዥን በማነጋገር ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል። በክልሉ ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት መካከል አለመግባባት መፈጠሩን መዘገባችን ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide