በጎሳ ግጭት ከ40 በላይ ሰዎች አለቁ ግጭቱ እንደቀጠለ ነው

ሰኔ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በቦረና ዞን አሬሮ ወረዳ ውስጥ በገብራና በቦረና ጎሳዎች መካከል በተነሳ ግጭት እስካሁን ድረስ ከ40 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል። ግጭ ቱ ዛሬ ድረስ የቀጠለ ሲሆን አድማሱን እያሰፋ መምጣቱንም የአካባቢው ሰዎች ለኢሳት ተናግረዋል።

የአካባቢው ሰዎች እንደሚናገሩት በእስካሁኑ ግጭት የዛሬውን ሳይጨምር ከገብራ 21 ከቦረና ደግሞ 19 ሰዎች ተገድለዋል። በዛሬው እለትም የውጊያው አድማስ ሰፍቶ ሱልሉታ ወደሚባለው የያቬሎ አካባቢ ተስፋፍቷል።

ሁለቱ የኦሮሞ ጎሳዎች ከዚህ በፊትም ደም አፋሳሽ የሆነ ውጊያ አድርገው ነበር ። አንድ የአካባቢው ሰው ሁለቱ ለዘመናት ተፋቅረው የነበሩት ህዝቦች በአሁኑ ጊዜ ወደ ደም አፋሽ ጦርነት የገቡት በኢህአዴግ የዘር ፖለቲካ የተነሳ ነው ይላሉ

የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ የፌደራል ፖሊስ እስካሁን ድረስ በአካባቢው ተገኝተው ውጊያውን ለማስቆም አለመቻላቸው የአካባቢውን ሰዎች አስቆጥቷል።

ከአራት ወራት በፊት የሶማሊ ተወላጆች በሆኑ ገሪዎችና የኦሮሞ ተወላጅ በሆኑት ቦረናዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በርካታ ሰዎች ማለቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጋሞ የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ በአርባ ምንጭና አካባቢዋ ውጥረት መኖሩን ዘጋቢያችን ገለጠ። በሲዳማ ዞን የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ሰሞኑን በአርባ ምንጭና አጎራባች ወረዳዎች ተመሳሳይ ችግሮች እየታዩ ነው። የፌደራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው መስፈራቸውን እና እያንዳንዱዋን እንቅስቃሴ በመቃኘት ላይ መሆናቸውን ዘጋቢያችን ገልጧል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከጎሳ ጋር በተያያዘ የሚነሱ አለመግባባቶች እየጨመሩ መምጣታቸው እየተነገረ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide