የአንድነት ፓርቲ የተቃውሞ ሰልፍ መተላለፉን ፓርቲው አስታወቀ

መጋቢት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ መስተዳድር ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ  ፓርቲው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የጠየቀባቸው ቦታዎች የተለያዩ ትምህርት ቤቶች እና ትላልቅ የመንግስት ተቋማት የሚገኙባቸው በመሆኑ እንዲሁም በእለቱ ሌሎች ተመሳሳይ የህዳሴ ግድብ ፕሮግራሞች ስለአሉ እውቅና እንደማይሰጥ ማሳወቁን ተከትሎ፣ አንድነት ፓርቲ የሰልፉን ቀን በአንድ ሳምንት አስተላልፏል።

ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የፓርቲው የአዲስ አበባ ጽ/ቤት ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ያሬድ አማረ ሰልፉ መተላለፉን ገልጸው በሚቀጥለው ሳምንት ሰልፉ ያለምንም ጥርጥር ይካሄዳል ብለዋል።

አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ የሚታዩት ማህበራዊ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፉ መምጣታቸውን በመቃወም ሰልፍ መጥራቱ ይታወቃል።