በጎንደር ከተማ በህገወጥ መንገድ ቤት ሰርታችሁዋል የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲያፈርሱ ተጠየቁ

መጋቢት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ 15 ሺ በላይ ህዝብ ይኖርበታል ተብሎ በሚገመተው ቀበሌ 18 በገንፎ ቁጭ ቀበሌ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸውን በአስቸኳይ እንዲያፈርሱ የታዘዘው ፣ ቤቱቹ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል በሚል ነው።

ቤቱቹ የተገነቡት ከ10 አመታት በፊት መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች መንግስት ቤቶቹ ሲሰሩ ማስቀም እየቻለ ዛሬ በአካባቢው አስፈላጊው ልማት ከተካሄደ በሁዋላ አፍርሱ ማለቱ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

በዛሬው እለት የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ መንግስት ፈቃድ ከልክሎአቸዋል። አካባቢው በፌደራል ፖሊስ የተከበበ በመሆኑም ውጥረቱ አይሏል።

ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የብአዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊዎችና የመዘጋጃ ሹሞች ቀርበው ህዝቡን ማነጋገራቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን ቤቱን አፍሩሰ ከማለት ውጭ ሌላ መፍትሄ ሳይሰጡዋቸው መሄዳቸውን ገልጸዋል።

“እኛ ኢትዮጵያዊያን አይደለንም ወይ፣ ልጆቻችንን የት እናድርጋቸው? በማለት አንድ ነዋሪ ምሬታቸውን ገልጸዋል ። ነዋሪዎች በ7 ቀናት ውስጥ ቤታቸውን ባያፈርሱ በሃይል እንደሚፈርስባቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ።