መስከረም ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በሟቹ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ምትክ የኢትዮጵያ ፓርላማ ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የቀረበለትን ዕጩ ጠ/ሚኒስትር ሹመት ተቀብሎ በማጽደቁ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር በትናንትናው ዕለት ቃለመሃላ ፈጽመዋል፡፡
ፓርላማው ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የቀረበለትን የሹመት ጥያቄ ተቀብሎ ያጸደቀበት ሒደት ግን ሕግና ሥርዓትን ያልተከተለ ነው በሚል አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች እየተቹት ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ ሹመት የቀረበበት አግባብ የፓርላማውን ክብር የሚነካ ነበር ያሉት
ባለሙያዎቹ ጠ/ሚኒስትሩን በፓርላማ አብላጫ ድምጽ ካለው ገዥ ፓርቲ አባላት መካከል እንደሚመረጥ ሕገመንግስቱ እንደሚደነግግ አስታውሰዋል፡፡ ይህ ሥርዓት ግን ተጥሶ ከፓርላማው ውጪ ባለ አካል መከናወኑ ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም ብለዋል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚኒስትር እንዲሆኑ ዕጩ አድርጎ ያቀረባቸው የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ምክርቤት በመሆኑ የፓርላማ አባላቱ አጨብጭበው ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ አለመቻላቸው ያሳዝናል ብለዋል፡፡
ትክክለኛው አካሄድ አብላጫ ድምጽ ከያዘው ፓርቲ (ኢህአዴግ) የፓርላማ አባላት መካከል ለጠ/ሚኒስትርነት ዕጩዎች ቀርበው በአባላቱ መካካል ክርክር ተደርጎ
ይበጃል፣የፓርቲውን ጥቅም ያስጠብቃል የተባለ ሰው መመረጥ ነበረበት ያሉት ባለሙያዎቹ ይህ አለመደረጉ የፓርላማ ሥርዓቱን ጭምር መናድ ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡ ኢሳት በሳምንቱ መግቢያ ላይ እንደዘገበው አቶ ሀይለማርያምን ስርአትና ህግን በመጣስ በጥድፊያ ለማሾም የተደረገው ጥረት መሰረታዊ ምክንያቱ የአሿሿም ሂደቱ ሁሉንም ፓርቲዎች ያረካ ባለመሆኑ ተቃውሞ ይገጥመዋል በሚል ስጋት ነው። የኢህአዴግ አባላት እጩዎችን እንዲያቀርቡ ያልተደረገውም በአሿሿም ሂደቱ ውስጥ አቶ በረከት ስምኦንና በዙሪያቸው የተሰባሰቡ ሰዎች የሰሩትን ስራ አንዳንድ የኢህአዴግ የድርጅት አባላት በተለይም የኦህዴድ አመራሮች ያልተጠበቀ ተቃውሞ ሊያነሱ ይችላሉ በሚል ስጋት መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ለአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ገልጠዋል።
ባለፈው ሳምንት የኢህአዴግ ምክርቤት ስብሰባ አድርጎ የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ከመረጠ በኃላ መግለጫ የሰጡት አቶ በረከት ስምኦን በግንባሩ አሰራር መሰረት አቶ ኃይለማርያም ጠ/ሚኒስትር፣አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠ/ሚኒስትር ይሆናሉ ሲሉ የሰጡት መግለጫ ትልቅ ስህተት እንደነበረ ባለሙያዎቹ በማስታወስ
ተችተውታል፡፡
ምክትል ጠ/ሚኒስትሩን የመምረጥ ሥልጣን የጠ/ሚኒስትሩ እንጂ የግንባሩ አልነበረም፡፡በአሁኑ ሰዓት ፓርቲና የመንግስት ሥራ ፈጽሞ መለየት በማይቻልበት ሁኔታ መደበላለቁ በግልጽ አፍጥጦ የሚታይበት ሁኔታ መኖሩ የሚያሳዝን ነው ይላሉ የህግ ባለሙያዎች፡፡
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከተመረጡ በኃላ ባደረጉት ንግግር “የአቶ መለስን ሌጋሲ ሳይበረዝ ይዘን እንቀጥላለን” ማለታቸው የአዲሱ አመራር ፍርሃትና በራስ ያለመተማመን ያሳየ ነው የሚል አስተያየት በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ተሰምቷል፡፡“በዚህ ተለዋዋጭ በሆነ ዓለም፣አንድን ራዕይ ሳይበረዝ ይዘን እንቀጥላለን ማለት ፈጽሞ ሊሆን የሚችል
አይደለም፡፡ምናልባትም ከፍርሃት የመነጨ ባዶ ተስፋ ነው” ሲሉ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
የግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑት ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጡት ፣ የአቶ ሀይለማርያም ሹመት የትግራዊያን የበላይነት በዝቷል የሚለውን ትችት ለማብረድ ተብሎ የተሰጠ ሹመት እንጅ በእውነተኛ ለውጥ ላይ የተመሰረተ አይደለም።
ለአቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ የተሰጠው ሹመት የይስሙላ እንጅ እውነተኛ አይደለም ያሉት ዶ/ር ብርሀኑ ምንም እንኳ የመከላከያ ጄኔራሎችን የሚሾሙት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ እንደሆኑ ቢናገርም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሳይሸሙ 34 ለሚሆኑ ብርጋዴር ጄኔራሎች የማእረግ እድገት ተሰጥቷል፣ ከእነሱም መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የትግራይ ተወላጆች ናቸው ብለዋል።
ንጉስን የሚሾሙና የሚያወርዱ ቡድኖች ከጀርባ ሆነው ስልጣኑን እንደሚቆጣጠሩት የገለጡት ዶ/ር ብርሀኑ ፣ አቶ ሐይለማርያም ስልጣናቸውን ተጠቅመው እርሳቸው በፈለጉት መንገድ ለመሄድ የጸጥታ ሀይሉንም መቆጣጠር እንዳለባቸው ገልጠዋል። ” አካሄዱ በሙሉ ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ የሚጠቅም ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ቁልፍ መሆኑን የገለጡት ዶ/ር ብርሀኑ፤ እስካሁን በታየው ሁኔታ ያህንን ጥያቄ አለመመለሱንም ገልጠዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ አቶ በረከት ስምኦን ስለ ነጻ ፕሬስ እንዲሁም ስለ ካድሬ ስልጠና ልምድ ለመቅሰም ወደ ቻይና አቅንተዋል። አቶ በረከት ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ከሆኑት ከ ሚ/ር ሊዩ ዩንሻን ጋር ስለመልካም አስተዳደር ፣ ስለ ፕሬስና ካድሬ ስልጠና ተወያይተዋል፣ ለወደፊቱም ሁለቱ አገሮች ተቀራርበው ለመስራት ቃል ገብተዋል።
ቻይና ኢሳትን የመሳሰሉ ጣቢያዎችን ለማፈን የሚውሉ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ለኢትዮጵያ እንደምታቀርብ ይታወቃል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide